ማንቸስተር ሲቲ ኤሊዮት አንደርሰንን የክለቡ ክብረ ወሰን በሆነ ዋጋ ለማስፈረም ተስማማ

ማንቸስተር ሲቲ ኤሊዮት አንደርሰንን የክለቡ ክብረ ወሰን በሆነ ዋጋ ለማስፈረም ተስማማ

የእንግሊዙ ክለብ ማንቸስተር ሲቲ፣ በዘንድሮ የክረምት የዝውውር መስኮት የዓመቱን ትልቁን ድርድር አጠናቋል።

ሲትዝኖቹ የኖቲንግሃም ፎረስት እና የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን ኮከብ የሆነውን አማካይ ኤሊዮት አንደርሰንን በክለቡ ታሪክ ከፍተኛ የተባለ የዝውውር ሂሳብ ለማስፈረም ተስማምተዋል።

የዝውውር ሂሳቡ 116 ሚሊዮን ፓውንድ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን ክለቡ ከዚህ ቀደም ለጃክ ግሬሊሽ ካወጣው የዝውውር ዋጋ በላይ ሆኗል።

የ23 ዓመቱ ተጫዋች በአሁኑ ሰዓት በአሜሪካ እየተካሄደ ባለው የዓለም ዋንጫ ላይ ከእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን ጋር እየተጫወተ ይገኛል።

ክለቦች ስምምነት ላይ በመድረሳቸው፣ የተጫዋቹ የህክምና ምርመራ በአሜሪካ ይከናወናል።

ሆኖም እንግሊዝ ከፓናማ ጋር የምታደርገው ወሳኝ ጨዋታ መቃረቡን ተከትሎ፣ ምርመራው በጥንቃቄ እና በውድድሩ ላይ ተጽዕኖ በማይፈጥር መልኩ እንዲከናወን ጥረት እየተደረገ ነው።

ማንቸስተር ሲቲ በአዲሱ አሰልጣኝ ኢንዞ ማሬስካ መሪነት እየገነባ ባለው አዲስ ፕሮጀክት ውስጥ አንደርሰንን የቡድኑ እምብርት ለማድረግ ታቅዷል።

ባለፉት ሁለት የውድድር ዓመታት በኖቲንግሃም ፎረስት አስደናቂ ብቃት ያሳየው ወጣቱ አማካይ፣ በኢትሃድ ስታዲየም የረዥም ጊዜ የቡድን መሪ እንዲሆን ይጠበቃል።

ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ