አበቃለት ሲሉ የሚጀምር፤ ደክሟል ሲሉ የሚበረታው ክርስቲያኖ ሮናልዶ

አበቃለት ሲሉ የሚጀምር፤ ደክሟል ሲሉ የሚበረታው ክርስቲያኖ ሮናልዶ

ገና አይፎን የሚባል ነገር አልተፈጠረም ነበር … ሞባይል ስልክ የሚባል መገናኛ እንደ ቅንጦት ይታይ በነበረበት ዘመን፣ አንድ ፖርቹጋላዊ ወጣት ሜዳ ላይ መተንፈስ የጀመረው በእግር ኳስ ነበር።

ዘመኑ የቴክኖሎጂ አብዮት ከመፈጠሩ በፊት ነው።

ማርክ ዙከርበርግ ፌስቡክን አልፈጠረም ነበር።

ዩቲዩብ የለም፣ ጉግል ለብዙዎች እንግዳ ነው፣ ኢንስታግራም ወይም ቲክቶክ አልተወለዱም።

በዛ ድቅድቅ የቴክኖሎጂ ዘመን፣ ይህ ሰው ሜዳ ላይ ይጨፍር ነበር።

ኳስን በጥበብ፣ በፍቅር፣ በእልህ እና በችሎታ ብቻ ይጫወታት ነበር።

ጊዜ ተለወጠ፤ ዓለም በቴክኖሎጂ ተሞላች።

ዛሬ ዩቲዩብ፣ ፌስቡክ፣ ኤክስ (ትዊተር)፣ ኢንስታግራም እና ቲክቶክ የዓለማችንን ትኩረት ገዝተውታል። ዓለም በዲጂታል ዓለም ውስጥ ስትዋጥ፣ እርሱ ግን አሁንም በሜዳው ላይ አለ።

ድህነትን በችሎታው ተረት ያደረገ፤ ስሙን ከዓለም ምርጥ ተጫዋቾች ዝርዝር ውስጥ በወርቅ ቀለም ያስቀረ፤ በ41 ዓመቱ፣ ወጣትነትን የሚያስንቅ ጉልበት ያለው፤ አበቃለት ሲሉት የሚጀምር፣ ደክሟል ሲሉት የሚበረታ፣ በማይበገረው መንፈሱ ዓለምን የሚያስደንቅ “የማሸነፍ ስብእና”።

ሮናልዶ ለእግር ኳስ ብቻ ሳይሆን፣ ለሕይወትም ትልቅ ትምህርት ነው።

ትናንት በልጅነት ተስፋ የጀመረው ጉዞ፣ ዛሬ በታሪክ ማህደር ውስጥ የማይረሳ አሻራ ሆኖ ቀጥሏል።

ይህ ክርስቲያኖ ሮናልዶ ነው። ከጊዜ በላይ የዘለቀ ጥበብ!

ትናንት ምሽት ፖርቹጋል ኡዝቤኪስታን 5ለ0 በረታችበት ጨዋታ ሁለት ጎሎችን አስቆጥሮ ከጨዋታው በኋላ በቴሌቪዥን መስኮት ለተቺዎቹ በሰጠው መልስ”አዎ ተመልሻለሁ፣ እንዳትረሱት” በማለት አቋሙን በግልጽ አስታውቋል።

ስለ ቡድኑ ትችት ሲጠየቅም”እኛ አንድ ነን፤ ሁሌም ከውጪ የሚወራው ወሬ እንደዚህ ነው። 23 ዓመት ሙሉ ለትችቶቼ መልስ የምሰጠው በዚህ መልኩ ነው። እንደዛሬው ከተጫወትን የሚያቆመን እንደሌለ እናውቃለን” ሲል ተናግሯል።

ጫማህን መስቀል አለብህ ለሚሉትም ምላሹ አጭር ናት”ሁሉም ሰው ጫማዬን መስቀል እንዳለብኝ ይናገራል፣ እኔ ግን አሁንም ያለሁበት ደረጃ ላይ ነኝ” በማለት የአምስት ጊዜ የባሎንዲኦር ተሸላሚው ክርስቲያኖ ሮናልዶ ምላሽ ሰጥቷል።

ሮናልዶ ማለት ይህ ነው! ዕድሜን እንደ ቁጥር፣ ትችትን እንደ ነዳጅ የሚጠቀም የማይበገር ስብዕና ባለቤት።

ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ