በአንዱዓለም ሰለሞን
የተወዳጁ የእግር ኳስ ስፖርት ታላቅ የውድርር መድረክ ነው፤ የዓለም ዋንጫ፡፡ በዚህ የውድድር መድረክ በርካታ ስመ ጥር ተጫዋቾች የውድድሩ ክስተት ሆነው ውድድሩን አድምቀዋል፡፡ ብዙዎችም ደግሞ በተለያየ ጊዜ ስለውድድሩ የሚሰማቸውን ገልጸዋል፡፡ የዓለማችን የምንጊዜም ምርጥ ተጫዋች የሆነው ብራዚላዊው ፔሌ በአንድ ወቅት እንዲህ ብሎ ነበር፡-
“የዓለም ዋንጫ ጥሩና ታላላቅ ተጫዋቾችን ለመለየት በጣም አስፈላጊው መንገድ ነው፡፡ ይህ የውድድር መድረክ የታላቅ ተጫዋቾች መለኪያ ነው፡፡”
“በዓለም ዋንጫ ላይ መገኘት አለባችሁ፡፡ በዓለም ዋንጫ ላይ ደግሞ ማንኛውም ነገር ሊከሰት ይችላል፡፡”
ይህን ያለው ደግሞ አርጀንቲናዊው ኮከብ ሊዮኔል ሜሲ ነው፡፡
በእርግጥ ሀገርን ወክሎ በዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ውድድር ላይ መገኘት በራሱ ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም፡፡ ይህ ለማንኛውም ተጫዋች ልዩ ስሜትን የሚፈጥር ክስተት ነው፡፡ ለምን ቢሉ፤ ይህ እግር ኳስ፣ በተለይም ደግሞ ተወዳጁ የዓለም ዋንጫ ነውና፡፡ ነገሩ ላንዲን ዶኖቫን እንዳለው ነው፡-
“የዓለም ዋንጫን አልወድም ያለ ሰው አጋጥሞኝ አያውቅም፡፡ የእግር ኳስ ስፖርት አድናቂ ሆነም አልሆነም ሁሉም ሰው የዓለም ዋንጫን መመልከት ይወዳል!”
የኖርዌይ ብሔራዊ ቡድንና የማንቸስተር ሲቲው የፊት መስመር ተጫዋች፣ ኤርሊንግ ሀላንድ ደግሞ እንዲህ አለ፡-
“በዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ላይ ተሳትፌ አላውቅም ነበር፡፡ አሁን ግን ለመጀመሪያ ጊዜ አደርገዋለሁ፡፡ ይህ እጅግ አስደናቂ ነው፡፡ ምናልባትም የሀገሬን ብሔራዊ መዝሙር ስዘምር አለቅስ ይሆናል!”
የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ምንም እንኳ የስፖርቱ ታላቅ የውድድር መድረክ ቢሆንም፣ በርካታ ዝነኛ ተጫዋቾች በውድድሩ ለመሳተፍ አልያም ዋንጫውን ለማንሳት አልታደሉም፡፡ በውድድሩ ካልተሳተፉ አልያም ተሳትፈው ዋንጫውን ማንሳት ካልቻሉት ታዋቂ ተጫዋቾች መካከል የኔዘርላንዱ የኳስ ጠቢብ ዮሀን ክራይፍ፣ ፈረናሳዊው ሚሼል ፕላቲኒ፣ አርጀንቲናዊው አልፍሬዶ ዲ ስቲፋኖ፣ የሰሜን አየርላንዱ ጆርጅ ቤስት፣ የሀንጋሪው ፌሬንስ ፑሽካሽ፣ የ1995ቱ የባሎንዶር አሸናፊ ላይቤሪያዊው ጆርጅ ዊሀ፣ የ5 ጊዜው የባላንዶር አሸናፊ ክርስቲያኖ ሮናልዶን ለአብነት መጥቀስ ይቻላል፡፡
ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ በውድድሩ በተጫዋችነት ተሳትፈው ዋንጫውን ከፍ ከማድረግ ባሻገር፤ የሀገራቸውን ብሔራዊ ቡድን በማሰልጠን ዳግም ዋንጫውን ያነሱ ተጫዋቾች ደግሞ አሉ፡፡ እዚህ ላይ በእስከ አሁኑ የውድድሩ ታሪክ ሶስት ተጫዋቾች ብቻ ስማቸው ይነሳል፤ ብራዚላዊው ማሪዮ ዛጋሎ፣ የጀርመኑ ፍራንዝ ቤከንባወር እና ፈረንሳዊው ዲዲየር ዴሻምፕ፡፡
ብራዚላዊው ተጫዋች ማሪዮ ዛጋሎ ከብራዚል ብሔራዊ ቡድን ጋር በመሆን (በተጫዋችነትና በአሰልጣኝነት) 4 ጊዜ የዓለም ዋንጫን ማሳካት የቻለ ዝነኛ ተጫዋች ነው፡፡
በ1950 በተካሔደው የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ አዘጋጇ ብራዚል በዑራጓይ ተሸንፋ ዋንጫውን ስትነጠቅ በታላቁ ማራካኛ ስታዲየም ታድመው መራራውን ሽንፈት በዐይናቸው ከተመለከቱት 200 ሺህ ተመልካቾች መካከል ታዳጊው ማሪዮ አንዱ ነበር፡፡
እ.ኤ.አ በ2013 ለቢቢሲ ስፖርት ይህን አስመልክቶ ሲናገር እንዲህ ብሎ ነበር፡-
“የዚያን ዕለቱ ትዝታ ፈጽሞ ከአእምሮዬ አይጠፋም!”
በእርግጥም ለእግር ኳስ የተለየ ትርጉምና ፍቅር ባላቸው ብራዚላዊያን ደጋፊዎች ዘንድ ይህ ቀን ጥቁር ጠባሳን ጥሎ ያለፈ ነበር፡፡ በርካታ የብራዚል ደጋፊዎችን በእንባ ካራጨው ከዚህ የዓለም ዋንጫ ስምንት ዓመታት በኋላ፣ ቢጫ ለባሾቹ በውድድሩ የታሪክ ድርሳን ላይ አዲስና ደማቅ ታሪክ ሊያጽፉ በመድረኩ ተከሰቱ፡፡ ማሪዮ ዛጋሎም በ26 ዓመቱ ለሀገሩ ብሔራዊ ቡድን የመሰለፍ ዕድል አግኝቶ በ1958ቱ የዓለም ዋንጫ ከቡድን አጋሮቹ ጋር በስዊድን ተገኘ፡፡
በውድድሩ የ17 ዓመቱን ተአምረኛ ተጫዋች (ፔሌን) ለዓለም ያስተዋወቀችው ብራዚል፣ በፍጻሜው ጨዋታ አዘጋጇን ስዊድንን 5ለ2 በመርታት ዋንጫውን ስታነሳ ማሪዮ ዛጋሎ አራተኛዋን ጎል ከመረብ አሳረፈ፡፡
ከዚያ በኋላ እስከ አሁን ባለው የውድድሩ ሂደት ብራዚል የዓለም እግር ኳስ ዋንጫን በማሸነፍ ከሀገራት በቀዳሚነት ስሟ ሲጠራ፣ ማሪዮ ዛጋሎ ደግሞ በዚያ ታሪክ ውስጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ካበረከቱ ተጫዋቾች መካከል አንዱ ለመሆን በቅቷል፡፡
ከአራት ዓመት በኋላ እ.ኤ.አ በ1962 ብራዚል በቺሊ የተዘጋጀውን ዋንጫ የቀድሞዋ ቼኮዝሎቫኪያን 3ለ1 በሆነ ውጤት አሸንፋ ዋንጫውን ስታነሳ ማሪዮ ዛጋሎ ለቡድኑ ውጤት ጉልህ ሚና ከነበራቸው ተጫዋቾች ውስጥ የሚጠቀስ ነበር፡፡
በወቅቱ ፔሌ ገና በጨዋታው ጅማሮ ጉዳት ያጋጠመው ሲሆን ማሪዮ ዛጋሎ በአንጻሩ በጊዜው አጨዋወት በአጥቂ ተጫዋቾች ብዙም ባልተለመደ መልኩ ወደ ኋላ እየተመለሰ የተከላካይ ክፍሉን በማገዝ ጭምር ለቡድኑ ውጤታማነት የጎላ ሚና ተጫውቷል፡፡
ማሪዮ ዛጋሎ በተጫዋችነት ዘመኑ ካሳካቸው ሁለት ዋንጫዎች ባሻገር እ.ኤ.አ በ1970 በሜክሲኮ በተካሄደው የዓለም ዋንጫ የምንጊዜም የብራዚል ምርጥ የተባለውንና ፔሌ፣ ጀርዚኖ፣ ካርሎስ አርቤርቶን እና መሰል ከዋክብትን የያዘውን ቡድን በአሰልጣኝነት በመምራት ዋንጫውን ማግኘት ችሏል፡፡
በዚህ የዓለም ዋንጫ፣ “ፕሮፌሰሩ” በሚል ቅጽል ስም የሚታወቀው የአሰልጣኝ ዛጋሎ ቡድን የመምራት ብቃትና ድንቅ የማጥቃት አቅም ያላቸው እንደ ፔሌ፣ ጃርዚንሆ፣ ገርሰን፣ ቶስታኦ እና ሪቬሊኖ ያሉ ተጫዋቾች እንቅስቃሴን የተቃራኒ ቡድኖች የሚቋቋሙት አልነበረም፡፡
እ.ኤ.አ በ1994 በአሜሪካ በተካሔደው የዓለም ዋንጫ በካርሎስ አርቤርቶ ፔሬላ የሚሰለጥነው የብራዚል ብሔራዊ ቡድን ጣሊያንን በመለያ ምት አሸንፎ ዋንጫውን ሲያነሳ ዛጋሎ የካርሎስ አርቤርቶ ፔሬራ እረዳት በመሆን ድሉን አጣጥሟል፡፡
ከዚህ ቀጥሎ አሰልጣኙ እ.ኤ.አ በ1998 በፈረንሳይ በተካሔደው የዓለም ዋንጫ የብራዚል ብሔራዊ ቡድንን በማሰልጠን እስከ ፍጻሜው የተጓዘ ቢሆንም በመጨረሻ ቡድኑ በፈረንሳይ ተረትቶ ዋንጫውን ሳያሳካ ቀርቷል፡፡
እ.ኤ.አ በ2002 በጃፓን እና ኮሪያ በተዘጋጀው የዓለም ዋንጫ ብራዚል በሉዊዝ ፊሊፕ ስኮላሬ እየተመራች ለ5ኛ ጊዜ ዋንጫውን ስታነሳ፣ ማሪዮ ዛጋሎ የአሰልጣኙ ልዩ አማካሪ በመሆን በውድድሩ ላይ ተገኝቶ ነበር፡፡
እ.ኤ.አ በ2006 የጀርመኑ የዓለም ዋንጫ ማሪዮ ዳግም የካርሎስ አልቤርቶ ፓሬላ ረዳት በመሆን ተከሰተ፡፡ ያም ሆኖ ብራዚል በሩብ ፍጻሜው በፈረንሳይ ተሸንፋ ከውድድሩ የተሰናበተች ሲሆን እርሱም ከዚያ በኋላ ራሱን ከስፖርቱ አገለለ፡፡
ለብራዚል ብሔራዊ ቡድን ብቻም ሳይሆን በአጠቃላይ ለእግር ኳስ ባለውለታ የነበረው ዝነኛው አሰልጣኝ በ92 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል፡፡ የብራዚሉ ፕሬዚዳንት ሉዊዝ ኢናሲዎ ሉላ ዳ ሲልቫ በወቅቱ፡-
“እርሱ ከምንጊዜም ታላቅ የእግር ኳስ ተጫዋቾችና አሰልጣኞች አንዱ ነበር” በማለት ተናግረዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ አስተያየታቸውን ሲቀጥሉም፡-
“… እርሱ ተስፋ አለመቁረጥን ካሳዩ ብራዚላዊያን አንዱ ነው፡፡ ለመላው ሀገራችንና ለዓለም እግር ኳስ ትቶት ያለፈውም ይህንኑ የፍቅር የቁርጠኝነትና ፈተናን የማሸነፍ መንፈስ ነው!” ብለዋል፡፡
ከማሪዮ ዛጋሎ በመቀጠል በዚህ ረገድ (በተጫዋችነትና በአሰልጣኝነት የዓለም ዋንጫን በማንሳት) ስሙ የሚነሳው ጀርመናዊው ተጫዋች ፍራንዝ ቤከንባወር ነው፡፡ እ.አ.አ በ1974 በምዕራብ ጀርመን የተዘጋጀውን ዋንጫ ራሷ ስታስቀረው ቤከንባወር ቡድኑን በአምበልነት መርቷል፡፡ በፍጻሜው ጨዋታ ምዕራብ ጀርመን የዩአን ክራይፏን ኔዘርላንድን 2ለ1 አሸንፋ የዋንጫ ባለቤት ስትሆን የቤከንባወር ሚና ከፍ ያለ ነበር፡፡
ይህ ከሆነ ከአስራ ስድስት ዓመታት በኋላ በ1990 ጣሊያን ባዘጋጀችው የዓለም ዋንጫ በስብስቧ ሉተር ማቲያስን እና አንድሬስ ብሬምን ያካተተችው ምዕራብ ጀርመን አርጀንቲናን 1ለ0 ረትታ ዋንጫውን ከፍ ስታደርግ ቡድኑን በአሰልጣኝነት መርቷል፡፡
ጀርመናዊው ተጫዋች በተጫዋችነቱም ሆነ በአሰልጣኝነት ዘመኑ ድንቅ ብቃቱን ማሳየት ችሏል፡፡ በተጫዋችነቱ በተለይም በመከላከል ረገድ አብዮት ያስነሳ የተባለለትን አዲስ የአጨዋወት ስልት ለዓለም ያስተዋወቀ ልዩ የእግር ኳስ ጥበበኛ ነው፡፡ እርሱ የሊበሮ ሚናን በአዲስ መልክ ማስተዋወቅ የቻለ ነው፡፡ እንደ ሊበሮ ተከላካይነቱ የተከላካይ ክፍሉን በብቃት ከመምራት ባለፈ፣ የማጥቃት እንቅስቃሴዎችን የማቀናጀት ነፃነትና ሚና ነበረው፤ ይህም ለጨዋታው ታክቲክ አዲስ ቅርጽ ሰጥቶታል።
ስለቤከንባወር ብቃት ምስክርነታቸውን ከሰጡ ተጫዋቾች መካከል ፖርቱጋላዊው ዩዞቢዮ እንዲህ ብሎ ነበር፡-
“እሱ በሁለቱም ቦታዎች (በተከላካይ ወይም በአማካይ ክፍል) መጫወት ይችል ነበር። ሁለገብና የመተጣጠፍ ብቃት ነበረው፡፡ ጨዋታውን በጥሩ ሁኔታ ማንበብና እንዴት መጫወት እንዳለበት ያውቃል፡፡ እንዲሁም ወደ ፊት በመሄድ ግቦችን ማስቆጠር ይችል ነበር፡፡”
እንግሊዛዊው ሰር ቦቢ ቻርልተን ደግሞ ተጫዋቹን እንዲህ ነበር የገለጸው፡-
«ፍራንዝ ቤከንባወር ድንቅ የኳስ አከፋፋይና ግሩም ተከላካይ፣ ሁልጊዜም ሁኔታዎችን ሙሉ በሙሉ የሚቆጣጠር እና በፍጹም የማይደናገጥ ተጫዋች ነበር።”
ሌላኛው መሰል ታሪኩን የምናነሳው ተጫዋች ደግሞ ወደ 1998ቱ ፈረንሳይ አዘጋጅታው ወደነበረው የዓለም ዋንጫ ይወስደናል፡፡
በዚህ የዓለም ዋንጫ ፍጻሜ አዘጋጇ ፈረንሳይ ከብራዚል ተገናኙ፡፡ ፈረንሳይም በዚነዲን ዚዳን ሁለት የማዕዘን ምት የጭንቅላት እና በኢማኑኤል ፒቲት ጎል ብራዚልን 3ለ0 በማሸነፍ ዋንጫውን አነሳች፡፡ በዚህ የፈረንሳይ ቡድን ውስጥ ደግሞ ዲዲየር ዴሻምፕ በአምበልነት ነበር፡፡
ይህ ታሪክ ከተፈጸመ ከ20 ዓመታት በኋላ በአዲሱ የፈረንሳይ ትውልድ በአሰልጣኝነት ተከሰተ፡፡ ይህ የሆነው ደግሞ በ2018ቱ ሩሲያ ባዘጋጀችው የዓለም ዋንጫ ነበር፡፡ ፖል ፖግባ፣ ኒጎሎ ካንቴ፣ አንቷን ግሬዝማን፣ ኦሊቨር ጂሩ እና ክሊያን ምፓፔ የተካተቱበት የፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን ስብስብም በፍጻሜው ጨዋታ ክሮሽያን 4ለ2 በመርታት ዋንጫውን አነሳ፡፡ ዲዲየር ዴሻምፕም በእስከ አሁኑ የውድድሩ ታሪክ በተጫዋችነትና በአሰልጣኝነት የዓለም ዋንጫን ካነሱ ሶስት ተጫዋቾች አንዱ ለመሆን በቃ፡፡
አሁን ብራዚላዊው ማሪዮ ዛጋሎ እና ጀርመናዊው ፍራንዝ ቤከምባወር በተወዳጁ የእግር ኳስ ስፖርት ታላቅ አሻራቸውን ጥለው አልፈዋል፡፡ ፈረንሳዊው ዲዲየር ዴሻምፕ ደግሞ ዛሬም የፈረንሳይን ቡድን እየመራ ይገኛል፡፡
አሰልጣኙ በመከናወን ላይ በሚገኘው 23ኛው የዓለም ዋንጫ የምድቡን የመጀመሪያ ጨዋታውን ከሴኔጋል ጋር አድርጎ 3ለ1 አሸንፏል፡፡

More Stories
ቼልሲ ማርኮ ፓሌስትራን ለማስፈረም ተስማማ
አበቃለት ሲሉ የሚጀምር፤ ደክሟል ሲሉ የሚበረታው ክርስቲያኖ ሮናልዶ
አርባምንጭ ከተማ ወደ ታችኛው ሊግ መውረዱ ተረጋገጠ