ቼልሲ ማርኮ ፓሌስትራን ለማስፈረም ተስማማ

ቼልሲ ማርኮ ፓሌስትራን ለማስፈረም ተስማማ

የእንግሊዙ ክለብ ቼልሲ የአታላንታውን የቀኝ መስመር ተከላካይ ማርኮ ፓሌስትራን ለማስፈረም ከስምምነት ላይ ደርሷል።

የምዕራብ ለንደኑ ክለብ ቼልሲ፣ ከቀናት በፊት ኢንተር ሚላን የዝውውሩን ሂደት እያጠናቀቀ ሳለ፣ በመጨረሻው ሰዓት ጣልቃ በመግባት ጣሊያናዊውን ጎበዝ የቀኝ መስመር ተከላካይ ማርኮ ፓሌስትራን ከአታላንታ እንደሚያስፈርም አረጋግጧል።

ቼልሲ ለ21 ዓመቱ ተስፈኛ ተጫዋች ከ55 ደሚሊዮን ዩሮ በላይ የሚገመት ጥቅል ክፍያ ለአታላንታ ለመክፈል ተስማምቷል።

በስምምነቱ ውስጥ የአታላንታን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ለወደፊት ተጫዋቹ ለሌላ ክለብ ሲሸጥ አታላንታ ድርሻ የሚያገኝበት አንቀጽ ተካቷል።

ምንም እንኳን ኢንተር ሚላን ከቀናት በፊት ከተጫዋቹ ወኪሎች ጋር የመጨረሻ የውል ስምምነት ላይ ደርሶ የነበረ ቢሆንም፣ የቼልሲ የገንዘብ አቅም እና የስፖርታዊ ፕሮጀክት ጥንካሬ አታላንታን እና ተጫዋቹን አሳምኗል።

አታላንታ በዚህ ክረምት በገበያ ላይ ያላቸው ብቃት የሚደነቅ ነው። ክለቡ ቀደም ብሎ ኤደርሰንን ወደ ማንቸስተር ዩናይትድ ለዝውውር ያቀረበ ሲሆን፣ አሁን ደግሞ ፓሌስትራን ወደ ለንደን በማቅናት ከሁለቱ ተጫዋቾች ብቻ ከ100 ሚሊዮን ዩሮ በላይ ገቢ በማሰባሰብ የዝውውር ገበያውን በበላይነት እየመራ ይገኛል።

አታላንታ ተስፈኛ ወጣት ተጫዋቾችን አፍርቶ በከፍተኛ ዋጋ በመሸጥ ረገድ በአውሮፓ እግርኳስ አርአያ እየሆነ ነው።

ማርኮ ፓሌስትራ በቅርብ ጊዜ በተለይም በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን በካግሊያሪ የነበረው የውሰት ቆይታው የእግርኳስ ዓለምን ትኩረት የሳበ ነበር።

እንደ አጥቂ በሚያገለግል መልኩ በክንፍ መስመሩ የሚጫወተው ፓሌስትራ፣ አሁን በቼልሲ የዘመናዊ እግርኳስ ታክቲክ ውስጥ ትልቅ ድርሻ እንደሚኖረው ይጠበቃል።

ቼልሲዎች ኢንተር ሚላንን በመቀማት ያገኙት ይህ ዝውውር፣ ለክለቡ የኋላ መስመር ጥንካሬ ትልቅ ተጨማሪ እሴት ይሆናል ተብሎ ታምኖበታል።

ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ