በዶሮ እርባታ ዘርፍ በመሰማራት የተሻለ ውጤት እያስመዘገቡ መሆናቸውን የየም ዞን ሣጃ ከተማ በዘርፉ የተሰማሩ ሰዎች ተናገሩ

በከተማው የዶሮ ምርታማነትን ለማሳደግ ሙያዊ ድጋፍና ክትትል ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ በየም ዞን የሳጃ ከተማ አስተዳደር ግብርና ዩኒት አስታውቋል።

በሳጃ ከተማ አስተዳደር ከሌማት ትሩፋት ዘርፍ አንዱ በሆነው በዶሮ እርባታ ከተሰማሩ መካከል ከ12 ዓመት ስደት በኋላ ወደ ሀገራቸው የተመለሱት ወ/ሮ ከድጃ ሚፍታ ተጠቃሽ ናቸው።

በሰጡት አስተያየትም የዶሮ እርባታ ስራ ከተሰራበት አትሪፊ ዘርፍ መሆኑን ከባለሙያዎች ግንዛቤ ማግኘታቸውን ጠቁመው፥ የእንቁላል እና ሥጋ ዶሮዎችን በማርባት የኢኮኖሚ አቅማቸውን ለማሳደግ ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ለሌላኛው የሳጃ ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ ጌታቸው ታከለ የመንግስት ሥራ ሠዓት በማያሻማ መልኩ የዶሮ እርባታ ሥራ እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የዶሮ መኖ ዋጋ ቢጨምርም ችግሩን ተቋቁመው እየሰሩ እንደሚገኙ የጠቀሱት አቶ ጌታቸው እየተደረገላቸው ያለው ድጋፍና ክትትል ደስተኛ እንደሆኑም ገልፀዋል።

በየም ዞን በሣጃ ከተማ የግብርና ዩኒት አስተባባሪ እና የኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪ ተወካይ ወ/ሮ ይርጋለም ኃይሉ፥ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በከተሞች የተጀመረው የልማት ትሩፋት ልማት ዘርፍ አንዱ በሆነው በዶሮ እርባታ ልማት ስራ የተሰማሩ ግለሰቦች ምርታማነታቸውን እንዲያሳድጉ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።

በበጀት ዓመቱ ከነባር ዶሮ በተጨማሪ 20ሺ 650 ጫጩት 25ሺ የሥጋ እና እንቁላል ዶሮዎችን በማርባት 45 ቶን የእንቁላል ምርት ማግኘት መቻሉን አስረድተዋል።

የሣጃ ከተማ ግብርና ዩኒት የእንስሣት እና ዓሣ ልማት ቡድን መሪ አቶ ተመስገን ሣርባ በበኩላቸው ከዚህ ቀደም በአከባቢው የሚያረቡ ማህበራትና ግለሰቦች ባለመኖራቸው ከቦንጋ እና ወልቂጤ በማምጣት ይወጣ የነበረውን ጊዜ፣ ጉልበት እና ገንዘብ ለመቅረፍ በሣጃ ከተማ 7 ኢንተርፕራይዞች ተደራጅቶ የአንድ ቀን ጫጩት እያሰራጩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የከተማ ነዋሪዎች ቢያንስ ከአምስት በላይ ዶሮ እንዲያመርት ግብ ተጥሎ እየተሰራ መሆኑንም ጠቅሰው፥ ወጣቱ ጠንክሮ በመስራት ኢኮኖሚ አቅማቸውን ማሳደግ እንዳለባቸውም መልዕክት አስተላልፈዋል።

ዘጋቢ፡ ማሙዬ ፊጣ – ከወልቂጤ ጣቢያችን