የከተማውን መሰረተ ልማት ከማሟላት ባሻገር ለነዋሪዎች ምቹ እና ማራኪ በማድረግ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

የከተማውን መሰረተ ልማት ከማሟላት ባሻገር ለነዋሪዎች ምቹ እና ማራኪ በማድረግ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ ሰኔ 17/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) የከተማውን መሰረተ ልማት ከማሟላት ባሻገር ለነዋሪዎች ምቹ እና ማራኪ በማድረግ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተሰራ መሆኑን በምስራቅ ጉራጌ ዞን መስቃን ወረዳ የዊጣ ታዳጊ ማዘጋጃቤት ጽህፈት ቤት ገለፀ።

ከተማው ወደ ታዳጊ ማዘጋጃነት ካደገ በኋላ የመብራት፣ የመንገድና የውሀ መሰረተ ልማቶች እየተስፋፉ መምጣታቸውም የከተማው ነዋሪዎች ተናግረዋል።

በምስራቅ ጉራጌ ዞን መስቃን ወረዳ የዊጣ ታዳጊ ማዘጋጃቤት ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አህመኑር ከድር እንደገለፁት የከተማው መሰረተ ልማት ከማሟላት ባሻገር ለነዋሪዎች ምቹ እና ማራኪ በማድረግ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተሰራ ነው።

በዚህም የ4.2 ኪ.ሜ መንገድ ጠረጋና ሬዳሽ የማልበስ ስራ ሰርተናል ያሉት ስራ አስኪያጁ በተጨማሪም 2.8 ኪ.ሜ የመብራት ዝርጋታ ስራ መከናወኑን አንስተዋል።

አክለውም የ3.7 ኪ.ሜ የውሀ መስመር ዝርጋታ እንዲሁም የተበላሹ የውሃ ቱቦዎችን የመጠገን ስራ መሠራቱንም ነው የገለፁት።

ለመዘጋጃው እድገት ህብረተሰቡ ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን በማንሳት ላደረገው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበው ድጋፉ አሁንም ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ሲሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

መዘጋጃው ከተመሰረተ ጀምሮ የማህበረሰቡን የመሠረተ ልማት ፍላጎት ለማሟላት እየሰራ መሆኑን ያነሱት የዊጣ ታዳጊ መዘጋጃ የ01 ቀበሌ ሊቀመንበር አቶ ጀማል ከማል፥ በበጀት አመቱ የሴራና፤ የንቡር፤ የአቦቸና፤ የወገሬት መንደሮችን የሚያገናኝ የውስጥ ለውስጥ መንገድ የሬዳሽ ማልበስ ስራ፣ ጥገና እንዲሁም የዲች ስራ በማከናወን ላይ መሆናቸውን ነው የጠቆሙት።

አቶ ጀማል አክለውም ማህበረሰቡንና ባለሀብቶችን በማስተባበር ከ280 ሺህ ብር በላይ በሆነ ወጪ ሶስት የአቅመ ደካሞች ቤት ገንብተው መስጠታቸውም አስታውሰዋል።

ማህበረሰቡ ለመንገድ ዝርጋታው ስራ ማሳውን በራሱ ፍላጎት እያነሳ መሆኑን በመጠቆም ይህም ለከተማዋ እድገትና ለልማት ያለው ፍላጎት ማሳያ ነው ብለዋል።

አግኝተን ያነጋገርናቸው የከተማው ነዋሪዎች በሰጡን አስተያየት ከተማው ላይ መዘጋጃ ከገባ በኋላ የመንገድ፣ የውሀና የመብራት ተጠቃሚ መሆናቸውን አንስተዋል።

ነዋሪዎቹ አክለውም ከዚህ በፊት ለመዘጋጃው የተለያዩ እገዛዎችን ሲያደርጉ መቆየታቸውን በማንሳት ወደፊት የሚያስፈልገውን ሀሉ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆናቸውን ገልፀዋል።

ዘጋቢ፡ አስፍር ሙህዲን – ከወልቂጤ ጣቢያችን