የዱራሜ ከተማ የኮሪደር ልማት ሥራ በአዲስ መልክ በዘመናዊ ዲዛይን እየተሰራ መሆኑን የዱራሜ ከተማ አስተዳደር ገለፀ

የዱራሜ ከተማ የኮሪደር ልማት ሥራ በአዲስ መልክ በዘመናዊ ዲዛይን እየተሰራ መሆኑን የዱራሜ ከተማ አስተዳደር ገለፀ

በጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አቢይ አሐመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጭነት የተጀመረው የኮሪደር ልማት ስራ ለከተሞች ውበትን ከማጎናፀፍ ባሻገር ለትራፊክ ፍሰት ቁጥጥርና ሁሉዓቀፍ የከተሞች ዕድገት ወሳኝ መሆናቸው ተመላክቷል።

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የዱራሜ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አክሊሉ አቡቶ እንደገለፁት በከተማው አሁን የተጀመረው የኮሪደር ስራ ከብዙ አካባቢዎች ከተሰሩ የኮሪደር ልማት ስራዎች ልምድ የተወሰደበት እና መጀመርያ የነበሩ የአፈፃፀም ውስንነቶችን በመለየት ወደ ተግባር የተገባበት ነው።

የኮሪደር ልማት ስራው ከከተማ ውበት ባሻገር ለተሽከርካሪዎችም ሆነ ለእግረኞች ምቹና የተስተካከለ እንቅስቃሴን የሚፈጥር ከመሆኑም በላይ፣ የሕፃናት መጫወቻዎችንና መዝናኛዎችን በማካተት ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች ፍትሐዊ የአገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።

የልማት ሥራዎች በቅንጅት መከናወን እንዳለባቸውና ጥራቱን የጠበቀ ልማት እንዲመጣ በጋራ መሥራት ያስፈልጋል ያሉት ከንቲባው፥ “ዱራሜን ለማሳደግ ሁላችንም በተባበረ ክንድ መረባረብ ይገባናል” ሲሉ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

ስራው በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ ጥራቱን ጠብቆ እንዲጠናቀቅ ለአምስት ኮንትራክተሮች ተከፋፍሎ መሰጠቱን የገለፁት ደግሞ አቶ ግዛቸው ገብሬ የዱራሜ ከተማ አስተዳደር ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ጽ/ቤት ምክትል እና የማስፈፀም ዘርፍ ኃላፊ ናቸው።

ስራውን ለመደገፍ መንግስት ስራተኞች ከደመወዛቸው እንዲሁም ባለሀብቶች ብሎም በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭ የሚኖሩ የዞኑ ተወላጆች ለአካባቢያቸው የራሳቸውን አሻራ እያስቀመጡ መሆኑ የሚበረታታ ህዝባዊ የልማት ተሳትፎ ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል።

የዱራሜን ከተማ ለኑሮ ምቹ፣ ለዓይን ማራኪ ማድረግ እንዲቻል ቅንጅታዊ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን አመላክተዋል።

በአዲስ መልክ የተጀመረው የኮሪደር ልማት ሁሉንም ዘመናዊ መዋቅሮች ያካተተና ከተማዋን በማስዋብ ከሌሎች የሀገሪቱ ከተሞች ጋር እኩል ተወዳዳሪ ለማድረግ ታስቦ የተወጠነ መሆኑን አንስተዋል።

ከተማዋን ለኑሮ ምቹ ለማድረግ በሚደረጉ ጥረቶች ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ጨረታውን አሸንፎ ወደ ሥራ የገባው የ”ሎራት ኮንስትራክሽን” ተቋራጭ ተወካይ ኢንጂነር አቤል ተፈራ በከተማው የተጀመረውን የኮሪደር ልማት ስራ በአጭር ጊዜ ውስጥ ጥራቱን በጠበቀ መልኩ ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

ዘጋቢ: አለማየሁ ማተቦ – ከሆሳዕና ጣቢያችን