“ማሽቃሮ” በዩኔስኮ ለማስመዝገብ በተደረገ ጥናት ላይ ውይይት እየተካሄደ ነው

“ማሽቃሮ” በዩኔስኮ ለማስመዝገብ በተደረገ ጥናት ላይ ውይይት እየተካሄደ ነው

ሀዋሳ፡ ሰኔ 16/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) የካፈቾ ዘመን መለወጫ በዓል (ማሽቃሮን) በዩኔስኮ ለማስመዝገብ በተደረገ ጥናት ላይ በቦንጋ ከተማ ውይይት እየተካሄደ ነው፡፡

የካፈቾ ዘመን መለወጫ በዓል (ማሽቃሮ) የባህል መዳረሻ ሆኖ በዩኔስኮ እንዲመዘገብ በባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የተጠና ጥናትን በተመለከተ ከባለድርሻ አካላት ጋር የመጀመሪያ ዙር የውይይት መድረክ እየተካሄደ ይገኛል።

የካፋ ዞን ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ ታሪኳ ታከለ በዘንድሮ ዓመት ከህዳር ወር ጀምሮ በባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የጥናት ቡድን ለጥናቱ የሚሆኑ ግብዓቶችና መረጃዎች ሲሰበሰቡ እንደነበር ተናግረዋል።

የጥናቱን የመጀመሪያ ደረጃ ውጤት ለማሳወቅና ቀሪ ስራዎችን ማጠናቀቅ በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ ለመመካከር የመድረኩ መዘጋጀት ፋይዳ እንዳለው ገልጸዋል።

የካፋ ዞን አስተዳደር ለጥናቱ እዚህ ደረጃ ላይ መድረስ አስተዋፅኦ ማበርከቱን ተናግረዋል።

የካፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳሻው ከበደ በበኩላቸው፥ የካፈቾ ዘመን መለወጫ በዓልን (ማሽቃሮን) በዩኔስኮ ለማስመዝገብ በጥናት የተደገፉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው ብለዋል።

በዓሉ በካፋ ዞን በማህበረሰቡ መካከል አንድነት እንዲጠናከርና ሠላም እንዲረጋገጥ አስተዋፅኦ ማበርከቱን ነው የተናገሩት።

በዚህም በክልሉ ባህል ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ በኩል ለፌደራል ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ቀርቦ ጥናት ሲደረግ መቆየቱን ጠቁመው፥ ባለፉት ዓመታት የሚኒስቴሩ አመራሮችና ባለሙያዎች በበዓሉ አከባበር ላይ እንዲገኙ መደረጉን አስረድተዋል።

ከእነኚህ ተግባራት መካከል አንዱ ይህ በዞኑ አስተዳደርና በየደረጃው ከሚገኙ የሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር በመከናወን ላይ የሚገኘው ይህ ጥናት ዋነኛው ነው ሲሉ ተደምጠዋል።

በዚህ መድረክ ውይይት ተደርጎ ግብዓቶች የሚገኙበት መሆኑን ገልጸው፥ ወደሚቀጥለው የስራ ምዕራፍ ለመሻገርና የሚፈለገውን ውጤት ለማግኘት የዞኑ አስተዳደር አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ ያደርጋል ብለዋል።

ማሽቃሮ በዩኔስኮ እንዲመዘገብ ለማድረግ በባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የተጠና ጥናት በጥናት ቡድኑ መሪ አቶ ማተቤ ጥላሁን እየቀረበ ይገኛል።

በመድረኩ የካፋ ንጉስ ኮላ ዎቾችን ጨምሮ የካፋ ዞን ከፍተኛ አመራሮችና የዞኑ ባህል አማካሪ ምክር ቤት አባላት እየተሳተፉ ነው።

ዘጋቢ፡ ዮሐንስ ክፍሌ – ከቦንጋ ጣቢያችን