በጎ ተግባር ወቅትን ጠብቆ የሚተገበር ብቻ ሳይሆን የሁልጊዜ ተግባራችንና ባህላችን ልናደርገው ይገባል -ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ

በጎ ተግባር ወቅትን ጠብቆ የሚተገበር ብቻ ሳይሆን የሁልጊዜ ተግባራችንና ባህላችን ልናደርገው ይገባል -ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ

ሀዋሳ፡ ሰኔ 16/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) በጎ ተግባር ወቅትን ጠብቆ የሚተገበር ብቻ ሳይሆን የሁልጊዜ ተግባራችንና ባህላችን ልናደርገው ይገባል ሲሉ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ገለጹ፡፡
‎”በጎነት ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል መሪ ቃል የ2018/19 ክልል አቀፍ የክረምት ወራት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ማስጀመሪያ ንቅናቄ በጋሞ ዞን ምዕራብ አባያ ወረዳ ቆላ ሙልአቶ ቀበሌ ተካሂዷል።

‎በመርሃ ግብሩ ማስጀመሪያ ላይ የተገኙት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ ብልጽግና በመደመር አዕማድ ዉስጥ በጎነትን ቁልፍ ተግባር አድርጎ በመተግበር ላይ ይገኛል ብለዋል።

‎ርዕሰ መስተዳድሩ አክለውም ወጣቶች ክረምቱን ከአልባሌ ተግባራት ተቆጥበው፤ በድንበር ተሻጋሪ የበጎ ተግባራት፥ የህዝብ ለህዝብ ትስስሮችንና የልማት ትብብሮችን የማጠናከር ስራዎችን ጨምሮ ፍቅር፣ ሰላምና አንድነትን አንግበው በተለያዩ ማህበራዊና የበጎ ፈቃድ ተግባራት በንቃት በመሳተፍ ዓርአያ ሆኖ መገኘት ይገባቸዋል ሲሉም በአጽንኦት ገልፀዋል፡፡

‎ባለፉት ስምንት አመታት የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን በየአመቱ በመስራት በኢትዮጵያ የታሪክ እጥፋት ማስመዝገብ እንደተቻለም ጠቁመዋል።

‎የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅ/ጽ/ቤት ኃላፊና የክልሉ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት አቢይ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ገ/መስቀል ጫላ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ከብልጽግና ፓርቲ የመደመር እሳቤ የሚመነጭ መሆኑን ተናግረው፥ ተግባሩ የተወሰኑ የማህበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ብቻ ሳይሆን ትዉልድን በመቅረፅ የነገዋን ታላቋን ኢትዮጵያ የሚገነባ እንደሆነም ጠቅሰዋል።

‎በክረምት ወራት በወጣቶች የሚከናወኑ ወሳን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባራት የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትና የሀገር አንድነትን የሚያጠናክሩ ተግባራት መሆናቸውን አስገንዝበዋል።

‎ባለፈው አመት በተከናወነው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት በክልሉ ከ15 ሺ በላይ ቤቶችን መገንባትና ማደስ እንደተቻለ አስታዉሰዉ፥ ዘንድሮም በተሻሻለው አሰራር መሠረት ቤቶች በብሎኬትና በጡብ ብቻ እንደሚገነቡ አስታዉቀዋል።

‎የክልሉ ወጣቶች ጉዳይና በጎ ፈቃድ አገልግሎት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ማርቆስ ማቴዎስ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የመደመር እና ሰዉ ተኮር እሳቤ መነሻ በማድረግ የሚከናወን ተግባር መሆኑን ገልፀዋል።

‎የገጠር ኮሪደር ልማት፣ የአረጋውያን ቤት እድሳት፣ የደም ልገሳ፣ አረንጓዴ አሻራ፣ ትምህርት፣ ጤናና የአካባቢ ጥበቃ ስራዎች ከተለዩ የትኩረት መስኮች ዋነኞቹ ናቸው።

‎በዘንድሮ በጎ ፈቃድ አገልግሎቱ 4 ነጥብ 8 ሚሊየን ህዝብ ተጠቃሚ ለማድረግና በዚህም4 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር ከመንግስት የሚወጣ በጀትን ለማዳን ታቅዶ እንደሚሰራ አስታውቀዋል።

‎የጋሞ ዞን አስተዳዳሪ ደምሴ አድማሱ(ዶ/ር)፥ በጎ ፈቃድ አገልግሎት የተቸገሩ ዜጎችን ለመደገፍ እና የከተማና የገጠር አካባቢዎችን ለማልማት ወሳኝ አጋጣሚ ነው ብለዋል።

‎የገጠር ኮሪደር ልማት፣ የአረጋውያን ቤት እድሳት፣ የደም ልገሳ፣ አረንጓዴ አሻራ፣ ትምህርት፣ ጤና፣ ኢትዮ ኮደርስና ፋይዳ፣ የአካባቢ ጥበቃ ስራዎች ከተለዩ የትኩረት መስኮች ዋነኞቹ መሆናቸው ተመላክቷል።

‎ዘጋቢ፡ ገነት መኮንን – ከአርባምንጭ ጣቢያችን