የእኛ ነገር

የእኛ ነገር

(ደስተኛ ያለመሆን)

ክፍል አንድ

በቦጋለ ወልዴ

እነሆ የያዝነውን ዘመነ 2ዐ15 ዓ.ም የሥራ ዘመን እንደየድርሻችን ተፍ! ተፍ እያልን ወደ አዲስ ዘመን ልንሻገር ምን ያህል ይቀረናል?! የቀሩት ከስምንት ሳምንታት የማይበልጡ መሆናቸውን ስናሰላ ኧረ ዘንድሮ ጊዜው ሮጧል! ሮጧል! ማለታችንን ልባችን ያውቀዋል፡፡

“ኑሮ” በተሰኘ ርዕስ በዶ/ር ኤርሲዶ ለንደቦ የታተመች መጽሃፍ ከውጪው የመጽሐፏ ልባስ “እያንዳንዱ ሰው የራሱ ህይወት ቀራፂ ነው!” የምትለዋ ብሂል ልቤን ገዝታዋለች፡፡ በእርግጥም በዘመን ጊዜ ዑደት እንዳቀድነው ተሳክቶልን ይሆን? ምኑ?! አትሉኝም? ውድ አንባቢዎቻችን፤ እንደአብነት – – – ፤

  • የግል የህይወት ጉዞአችን፣
  • የተጣሉብንን መደበኛና የዕድል ፈንታ ሥራዎቻችን ስኬታማነት፣
  • ከተግዳሮታችንስ ምን ገበየን? አስደስቶናል? ወይንስ? – – –

ዶ/ር ጆሴፍ ሙርፒ “The cosmic en­ergizer Miracle power of the universe” የሀገራችን ምሁር ተርጓሚ ብዙአየሁ አያሌው “የአሸናፊነት ሥነ ልቦና” በሚል ርዕስ በ2ዐ13 ዓ.ም ያስቀመጠውን ዐቢይ ቁምነገር ለማጋራት እነሆ ወድጃለሁና – – ዋናው ሰላም! ጤና! ተስፋ! በጐ በጐ ሁሉ አይለየን ብያለሁ። ከላይ ለጠቀስኩት ዋቢዬም ከወዲሁ በአንባቢያን ስም ምስጋናዬ ይድረስ፡፡

ደስተኛ አለመሆን ለምን ይመረጣል?

ብዙ ሰዎች ደስተኛ አለመሆን ምክንያቱ ራሳቸው የሚመርጡትን በቅጡ ካለማወቃቸው የተነሣ ነው፡፡ ከእነዚህም ድርጊቶች ወይም አመለካከቶች መካከል በማለት ከዚህ በታች ያሉትን አስተሳሰቦች አቅርቦልናል፡፡

የዛሬው ቀን ጨለማ ነው፡፡ ምንም ሣይቀናኝ ነው የምውለው፣

• ዛሬ የሚሳካልኝ አይመስለኝም፣

• ሁሉም ሰው ከኔ በተቃራኒ ነው የተሰለፈው፣

• ሁሌም ወደ ኋላ የቀረሁ ነኝ፣

• እሱ /እሷ/ ይሳካለታል (ይሆንለታል) እኔ ግን አይሳካልኝም፡፡

ጠዋት ከእንቅልፍህ ስተነሣ (ስትነቃ) በእነዚህ አስተሳሰቦች ውስጥህ ተሞልቶ ከሆነ እነዚህና መሰል አስተሳሰቦችና ተሞክሮዎችን ወደ ራስህ ትስባቸዋለህ፡፡ በዚህም መነሻ ፈፅሞ ደስተኛ ልትሆን አትችልም፡፡

የምትኖርበት ዓለም ቅርፅና ይዘቱ የሚወሰነው አእምሮህ ውስጥ በሚፀነሰው ሀሳብ መሆኑን ተረዳ፡፡ ታላቁ የሮማ ፈላስፋና ጠቢብ ማርክስ ኬሊሲየስ እንዲህ ብሎ ነበር። “የሰው ልጅ ህይወት የሃሳቡ ውጤት ነው”

የ19ኛው ምዕተ ዓመት አሜሪካዊው ኤመርሳንም “አንድ ሰው ቀኑን ሙሉ የሚያስበውን ነው የሚሆነው” ብሏል፡፡ በአእምሮ ውስጥ ልማድ ሆነው የተቀመጡ እሳቤዎች አንተን በአካል የመግለፅ ወይም በገሃዱ ዓለም እንድታንፀባረቅ የማድረግ አቅም አላቸው፡፡

“ስለሆነም የሚያስጨንቁ፣ የሚያስከፉ እንዲሁም የሚያበሳጩ አሉታዊ ሀሳቦችን ወደ አእምሮህ እንዳይገቡ ነቅተህ ጠብቅ። ከአስተሳሰብህ ውጪ ምንም ነገር እንደማይገጥምህ አስታውስ።” የሚለን ይኸው ተርጓሚ ብዙአየሁ አያሌው እንደሚከተለውም በንዑስ ርዕሱ ያመላክተናል፡፡

አንድ ሚሊዮን ዶላር ቢኖረኝ ኖሮ ደስተኛ እሆን ነበር ሀብታም መሆንና ሀብት በራሱ ደስተኛ አያደርግም፡፡ በሌላ መልኩ ሀብት ደስተኛ ለመሆን መተማመኛ አይደለም። ዛሬ ዛሬ በርካታ ሰዎች የተለያዩ ቁሳ ቁሶችን እንደ ኤችዲ ቴሌቪዥን፣ ዘመናዊ አውቶሞቢሎችን፣ በዲዛይነር የተሰሩ አልባሳቶችን ወዘተ ለመግዛትና ደስታን ለመሸመት ይጥራሉ፡፡ ይሁን እንጂ ደስታን በዚያ መልክ መሸጥም መለወጥም አይችሉም።

የደስታ ግዛቱ በሃሳብህና በስሜትህ ውስጥ ነው፡፡ በርካታ ሰዎች ደስታን ለመፍጠር የሆነ አርተፊሻል ነገር ጣል መደረግ አለበት ብለው ያምናሉ፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ “የዚህ ከተማ ከንቲባ ሆኜ ብመረጥ፣ የዚህ ድርጅት ኘሬዝዳንት ሆኜ፣ በአንድ የማህበረሰብ ጋዜጣ የፊት ገፅ ላይ ስሜ ቢወጣ ወዘተ ደስተኛ እሆን ነበር” ይላሉ፡፡ ነገር ግን እውነታው ደስታ አእምሮአዊና መንፈሳዊ ኑባሬ መሆኑ ነው፡፡

ቀደም ሲል ከተጠቀሱት አንዳቸውም ደስታን ለማግኘት የግድ መሟላት ያለባቸው ቅድመ ሁኔታዎች አይደሉም፡፡

ጥንካሬህ ሰላምህ በውስጠ ህሊናህ ውስጥ ተጨባጩን መለኮታዊ ስርዓትና ትክክለኛ ድርጊትን በመከተል የሚገኙ ናቸው። በዚህም እነዚህን መርሆች በየትኛውም የህይወት ክፍል ላይ ተግባራዊ አድርጋቸው በማለት ተጨማሪ ንዑስ ርዕስ ይጋብዘናል ተርጓሚው።

ደስተኛነት ከሰላማዊና ከተረጋጋ አእምሮ የሚገኝ መሆኑ የገባው ከአመታት በፊት፣ በሳንፍራንሲስኮ ስለ ደስተኛነት ትምህርት ስሰጥ በስራው የተማረረ ወይንም ደስተኛ ያልሆነ ሰው አነጋግሬ ነበር፡፡ ይህ ሰው ታዲያ በሚሰራበት ድርጅት ውስጥ ዋና ስራ አስኪያጅ የነበረ ሰው ነው፡፡

የዚህ ሰው ኩባንያ ትርፋማነት አሽቆለቆለ።

ይኸ ሰው ታዲያ በኩባንያው የተከሰቱትን “የቢዝነስ” ችግሮች በዚህ መልኩ ነበር እልባት ያስገኘለት በማለት እንደሚከተለው ያሳየናል። የመጀመሪያው ነገር ዘወትር ማለዳ ከእንቅልፉ ሲነቃ በንፁህ አእምሮ ለራሱ እንዲህ ሲል ቃል ገባ፡-

“በድርጅታችን ውስጥ ያሉ ሠራተኞች በሙሉ ቅን፣ እውነተኛና በጐ አሳቢዎች እንዲሁም በጋራ ተባብሮ ለመስራት ዝግጁዎች ናቸው፡፡ በዚህ ድርጅት የእድገት ሰንሰለት ውስጥ አእምሮአዊና መንፈሳዊ አጣማሪዎች ናቸው፡፡

ለሁለቱ የሥራ ባልደረቦቼም ሆነ ለተቀሩት የድርጅቱ ሠራተኞች በመላ በሃሳቤ፣ በቃላቶቼና በድርጊቶቼ ፍቅር፣ ሰላምና መልካምነትን እገልፃለሁ፡፡

የድርጅታችን ኘሬዝዳንትና ምክትሉ በስራቸው ሁሉ መለኮታዊ ምሬት ያላቸው ናቸው። የውስጠ ህሊናዬ ጥበብና አስተውሎም በእኔ አማካኝነት ሁሉንም ይወስናል፡፡ ይህም የሚሆነው በስራችንና እርስ በእርሳችን ሊኖረን የሚችለው መልካም ውጤት ብቻ ነው። ከእኔ በፊት ወደ ስራ ቦታዬም የሰላምና የፍቅር እንዲሁም የመልካምነት መልዕክቶችን እልካለሁ፡፡ በዚህም ሰላምና መተባበር እኔንም ጨምሮ በማንኛውም ሰራተኛ ልብና አእምሮ ውስጥ ከፍ ያለ ስፍራን ይይዛሉ፡፡

በመሆኑም እኔ አሁን አዲሱን ዕለት በሙሉ እምነት፣ ተስፋና በራስ በመተማመን እጀምራለሁ።

ይህ “የቢዝነስ” ሰው ከላይ የሰፈረውን ሀሳብ ዘወትር ማለዳ ለሶስት ጊዜ ያህል በጥሞና የመልዕክቱን እውነትነት እየተሰማው ሲደጋግም ቆይቷል፡፡

የፍርሃት ወይም የብስጭት ስሜቶችና ሃሳቦች ወደ አእምሮው ሲመጡ ለራሱ እንዲህ ይላል። “ሰላም፣ ደስታ፣ ህብር እንዲሁም የአእምሮ መረጋጋት አእምሮዬን ይገዛዋል።” አእምሮውን በዚህ መልኩ መምራቱን ሲቀጥል ሁሉም አሉታዊ እሳቤዎች ላይመለሱ ድራሻቸው ይጠፋል፡፡ በምትኩም ሰላም ወደ አእምሮው ይመጣል፡፡ አዝመራውን ሰበሰበ ማለት ነው፡፡

የመፅሐፏ ተርጓሚ እንደሚከተለው ሲያትት፡- “ይህን አስመልክቶ አእምሮውን ቅርፅ ባስያዘና በጋራ በሁለተኛው ሣምንት መጨረሻ በፃፈልኝ ደብዳቤ ላይ እንዳመለከተኝም የኩባንያው ኘሬዚዳንትና ምክትሉ ወደ ቢሮአቸው ጠርተውኝ ለስራ ትጋቴና ለአዳዲስ የፈጠራ ሃሳቦቼ አመሰገኑኝ” ይላል፡፡ እሱን በዚህ ኩባንያ ውስጥ በዋና ስራ አስኪያጅነት በማግኘታቸው የተሰማቸውን ክብርና ኩራት እንደገለፁለትም ይናገራል፡፡ በዚህም ከፍተኛ ደስታን መጐናፀፍ ችሏል፡፡

ደስተኛ ያለመሆን ከፊል ምርጫው ለካስ በእኛው ዘንድ ይወሰናል!!