ቅንጅታዊ የአሠራር ሥርዓት በመዘርጋት የፈተና አሰጣጥ ሥርዓትን በማዘመን ለተማሪዎች ውጤት መሻሻል በትኩረት እየተሠራ መሆኑ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ ሰኔ 03/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) ቅንጅታዊ የአሠራር ሥርዓት በመዘርጋት የፈተና አሰጣጥ ሥርዓትን በማዘመን ለተማሪዎች ውጤት መሻሻል በትኩረት እየተሠራ መሆኑን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አልማው ዘውዴ አስታወቁ፡፡

“የዘመነ ፈተና አስተዳደር ስርዓት፣ ለላቀ የትምህርት ጥራት!” በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀ የ2018 ዓ.ም ሀገራዊና ክልላዊ ፈተና አስተዳደር ምክክር መድረክ እየተካሄደ ይገኛል።

ያለፉ ዓመታት የፈተና አሰጣጥ ሥርዓትን በመገምገም የተያዘውን የትምህርት ዘመን ዝግጅት የፈተና አሰጣጥ ሥርዓትን በማዘመን የተሻለ ውጤት እንዲመዘገብ የሚያስችል የባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ የምክክር መድረክ በቦንጋ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።

በዚህ የምክክር መድረክ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አልማው ዘውዴ እንደገለፁት፥ በአገራችን የትምህርት ዘርፍ ልማት ውጤታማነትን ለማረጋገጥ እንዲቻል የትምህርት ሴክተር ሪፎርም ሥራዎች ሲሠሩ ቆይተዋል።

የትምህርት ጥራት ለማሻሻል የፈተና አስተዳደር ሥርዓት ማዘመን፣ የትምህርት ግብኣት ማሟላት፣ የመምህራን አቅም ማሻሻልና መሠል ሥራዎች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ እንዳለም አብራርተዋል።

የተማሪዎች ውጤታማነትን ለማረጋገጥ የፈተና አሰጣጥ ሥርዓት በማዘመን፣ የምዘናው ሥርዓት ደረጃ ያለበትን በማሣወቅ ካለፉት ዓመታት ይልቅ አሁን ላይ በተቀናጀ ርብርብ እየተሠራ መሆኑንም ገልጸዋል።

እንደ ክልል 17 ሺህ 458 ተማሪዎች የ12ኛ ክፍል የማጠናቀቂያ ፈተና የሚወስዱ ሲሆን ከእነዚህ ተማሪዎች መካከል 2030 ዲጂታል ኢትዮጵያ እውን ለማድረግ ክልሉ ካለው አቅም በመነሣት 9 ሺህ 602 ተማሪዎች በተለዩ 19 የፈተና ማዕከላት በበይነ መረብ ፈተና የሚወስዱ ናቸው።

89 ሺህ 538 ተማሪዎች ለ6ኛና ለ8ኛ ክፍል የተዘጋጁ ፈተናዎችን ይቀበላሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ገልጸዋል።

32 ሺህ 489 የ8ኛ ክፍል ተማሪዎች በበይነ መረብ ይፈተናሉ።

በሁሉም የክፍል ደረጃዎች ክልላዊና አገራዊ በተሻለ ሁኔታ የፈተና የዝግጅት ሥራዎች ሲሠሩ መቆየታቸውን አስረድተዋል።

በመድረኩ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ነጋሽ ዋጌሾን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ የአመራሮች፣ በክልሉ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንቶችና የየኮሌጆች ኃላፊዎች፣ የየዞኑ፣ የየወረዳው ዋና አስተዳዳሪና የየትምህርት መምሪያና ጽሕፈት ቤት ኃላፊዎች፣ የየፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊዎችና የባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ይገኛሉ።

ዘጋቢ፡ መሣይ መሠለ – ከቦንጋ ማስተባበሪያ