22ኛ መደበኛ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ስብሰባ ውሳኔዎች

22ኛ መደበኛ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ስብሰባ ውሳኔዎች

የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው 22ኛ መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ፡፡

1. በቅድሚያ ምክር ቤቱ የተወያየው በመንግስት ሚስጥራዊ መረጃዎች ምደባ እና ጥበቃ ረቂቅ ደንብ ነው፡፡
2. የመንግስት ሚስጥራዊ መረጃዎችን በማስተዳደር እና ጥቅም ላይ በማዋል ረገድ የተለያዩ የመንግስት ተቋማት፣ የመንግስት ኃላፊዎችና ሠራተኞች እንዲሁም በተለያየ መልኩ መረጃው ተደራሽ የሆነላቸው አካላት መብትና ግዴታዎች በግልፅ መደንገግ በማስፈለጉ፤ ሚስጥራዊ መረጃዎችን በኤሌክትሮኒክስ ዘዴዎች ለመለዋወጥ የተዘረጋ ስርዓት ባለመኖሩ በየደረጃ ያሉት የመንግስት አመራሮች እና ሰራተኞች እራሳቸው በመረጡትና ደህንነታቸው ባልተረጋገጠ መረጃ መለዋወጫ ቴክኖሎጂዎች የሚጠቀሙ በመሆኑ የአገሪቱን ደህንነትና ሉዓላዊነት ለአደጋ የሚያጋልጥ እንዳይሆን መከላከል በማስፈለጉ፤ የመንግስት ሚስጥራዊ መረጃዎችን ለመመደብ የሚያስችል ግልፅ እና ተጠያቂነት የሰፈነበት የአሠራር ስርዓት መዘርጋት እንዲሁም መረጃዎቹ በህገወጥ መንገድ ይፋ እንዳይሆኑ፣ እንዳይጠፉ፣ እንዳይለወጡ እና እንዳይተላለፉ ተገቢውን ጥበቃ ለማድረግ የሚያስችል ረቂቅ ደንብ ተዘጋጅቶ ለምክር ቤቱ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በረቂቅ ደንቡ ላይ በሰፊው ከተወያየ በኋላ ግብዓቶችን በማከል በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት ቀን ጀምሮ በስራ ላይ እንዲውል በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡
3. በመቀጠል ምክር ቤቱ የተወያየው የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ምርቶች የደህንነት ማረጋገጫና ቁጥጥር ረቂቅ አዋጅ ላይ ነው፡፡

ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ እና ከሀገር የሚወጡ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ምርቶች በሀገር የመረጃ ደህንነት ላይ የሚያስከትሉትን አሉታዊ ተፅዕኖ ለመከላከልና ለመቆጣጠር ፣ ተገቢው ቁጥጥር ያልተደረገባቸው የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ምርቶች በሀገር ደህንነት ላይ ሊያደርሱ በሚችለው አሉታዊ ተፅዕኖ ላይ ዜጎች በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸው የሚያስችል፣ መብትና ግዴታዎችን በግልፅ የሚደነግግ፣ ስጋት ለሚፈጥሩ ድርጊቶች ተገቢና ተመጣጣኝ እርምጃ መውሰድ የሚያስችል ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በረቂቅ አዋጁ ላይ በሰፊው ከተወያየ በኋላ ግብዓቶችን በማከል በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲጸድቅ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡

4. ሌላው ምክር ቤቱ የተወያየው የኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ባለስልጣን ሰራተኞች አስተዳደር ረቂቅ ደንብ ላይ ሲሆን የካፒታል ገበያ ለአገራችን አዲስ በመሆኑና ከስራው ውስብስብነት አንጻር ሰራተኞቹን መመልመልና ማስተዳደር እንዲቻል፣ ሚዛኑን የጠበቀ የሠራተኛ አስተዳደር እንዲኖር እና ሰራተኞች መብትና ግዴታቸውን አውቀው ዘርፉ የሚጠይቀውን የሥራ ኃላፊነትና ዲሲፕሊን ጠብቀው እንዲገኙ የሚያስችል ስርዓት መዘርጋት የሚያስችል ረቂቅ ደንብ ተዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በረቂቅ ደንቡ ላይ ከተወያየ በኋላ ግብዓቶችን በማከል በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት ቀን ጀምሮ በስራ ላይ እንዲውል በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡

5. በተጨማሪም ምክር ቤቱ ኢትዮ-ባዮፋርማ ግሩፕን እና ሽልድቫክስ ኢንተርፕራይዝን ለማቋቋም የቀረቡ ረቂቅ ደንቦች ላይ ተወያይቷል፡፡ ኢትዮ-ባዮፋርማ ግሩፕ በአገራችን ያለውን የሰው እና የእንስሳት ክትባቶች፤ መድኃኒቶች፤ የሕክምና መገልገያዎችና መሳሪያዎች፣ እንዲሁም ተዛማጅ ምርቶችን በማምረት የውጭ ምንዛሪ ወጪን መቀነስ ብሎም ለጎረቤት አገራት ተደራሽ ማድረግ የተቋቋመበት አላማ ሲሆን አላማውን ለማሳካት የሚያስፈልጉትን ሌሎች የልማት ድርጅቶች ለማቋቋም እና ለማስተዳደር የሚያስችል ስልጣን የሚሰጠው ረቂቅ ደንብ ተዘጋጅቶ ቀርቧል፡፡ በሌላም በኩል ሽልድቫክስ ኢንተርፕራይዝ በኢትዮ-ባዮፋርማ ግሩፕ ባለቤትነት የሚተዳደር በሰዎች ጤና ላይ ብቻ በማተኮር ክትባቶችንና ተዛማጅ ምርቶችን በማምረት ለአገር ውስጥ እና ለውጭ ገበያ የሚያቀርብ፣ በእውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር ላይ የሚሰራ ኩባንያ እንዲሆን የሚያስችለው ረቂቅ ደንብ ተዘጋጅቶ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በሁለቱም ረቂቅ ደንቦች ላይ በሰፊው ከተወያየ በኋላ ግብዓቶችን በማከል በነጋሪት ጋዜጣ ታትመው ከወጡበት ቀን ጀምሮ በስራ ላይ እንዲውሉ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡

ምንጭ ፡ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት