የትምህርት ቤቶችን ደረጃ የማሻሻል መርሀግብር በጌዴኦ ዞን በዲላ ከተማ ተጀመረ

የትምህርት ቤቶችን ደረጃ የማሻሻል መርሀግብር በጌዴኦ ዞን በዲላ ከተማ ተጀመረ

ሀዋሳ፡ ሐምሌ 11/2015 ዓ.ም (ደሬቴድ) የትምህርት ቤቶችን ደረጃ የማሻሻል መርሀግብር በጌዴኦ ዞን በዲላ ከተማ ተጀምሯል።

የትምህርት ቤቶችን ደረጃ የማሻሻል መርሀግብር በጌዴኦ ዞን በዲላ ከተማ ዳዊት ትምህርት ቤት ተጀምሯል።

በትምህርት ጥራት ላይ የተስተዋለውን ስብራት ለመጠገን በሀገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረው የትምህርት ቤቶች ማሻሻያ መርሀ ግብር ወሳኝነት እንዳለውም ነው የተገልጸው።

መድረኩን በንግግር የከፈቱት የዲላ ከተማ ከንቲባ አቶ ተስፋጽዮን ዳካ እንደተናገሩት፣ አሁን ለገጠመን የትምህርት ጥራት ስብራት ትምህርት ቤቶቻችን ማሳያዎች መሆናቸውን ጠቁመው የገጠመንን ስብራት ለመጠገን ህዝባችንን በማስተባበር ጠንካራ ሥራ እየተሠራ ነው።

አሁን የገጠመን ችግር የትምህርት ሥርዓት ችግር አይደለም ያሉት የጌዴኦ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ዘማች ክፍሌ በበኩላቸው የትምህርት ቤቶች ለመማር ማስተማር ምቹ አለመሆን፣ በርካታ ትምህርት ቤቶች ከደረጃ በታች መሆን፣ የግብዓት እጥረት እና የአንዳድ መምህራን ብቃት ማነስ ዋነኞቹ ችግሮች ናቸዉ ብለዋል።

አክለውም አቶ ዘማች  በዞኑ ውስጥ ከሚገኙ 2 መቶ 82 የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መካከል 94.9 በመቶ እና ከ 25 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መካከል 94.2 በመቶ ከደረጃ በታች መሆኑን በመጠቆም፣ በዞኑ ካሉት ከ4 ሽህ 7 መቶ 52 የመማሪያ ክፍሎች ውስጥ 3ሽህ 7መቶ 50 የመማሪያ ክፍሎች ከደረጃ በታች እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የጌዴኦ ዞን አስተዳዳሪ አቶ አብዮት ደምሴ ከዚህ በፊት ትኩረት የተነፈገው የትምህርት ሥራ  ከአሁን በኋላ ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫችን ይሆናል ያሉ ሲሆን ለዚህም የልማቱ ባለቤት የሆነውን ህዝብ በማስተባበር ጠንካራ ሥራ ለመሥራት ተዘጋጅተናል ብለዋል።

ዘጋቢ፡ አብነት አበበ – ከፍስሃገነት ጣቢያችን