አርሰናል ለሚኬል አርቴታ ከፍተኛ የደመወዝ ጭማሪ ሊያደርግ ነው

አርሰናል ለሚኬል አርቴታ ከፍተኛ የደመወዝ ጭማሪ ሊያደርግ ነው
 
አርሰናል የ22 ዓመታት የዋንጫ ጥማትን በመቋጨቱ ለሚኬል አርቴታ እውቅና ለመስጠት ስፔናዊውን አሰልጣኝ በዓለም ላይ ከፍተኛ ተከፋይ አሰልጣኝ ከሆኑት ተርታ የሚያሰልፍ አዲስና አትራፊ ውል ሊያቀርብለት ነው።
 
አርሰናል ዘንድሮ ከማንቸስተር ሲቲ ጋር በፕሪምየር ሊጉ ሲፎካከር በነበረበት ወቅት የአርቴታን የኮንትራት ማራዘሚያ ንግግር ለጊዜው ተቋርጦ የነበረ ቢሆንም፤ የውስጥ አዋቂዎች ግን ቡድኑ የውድድር ዘመኑን ያለ ዋንጫ ቢያጠናቅቅ እንኳ አርቴታ በክለቡ እንደሚቆይ በልበ ሙሉነት ይናገሩ ነበር።

የ44 ዓመቱ አርቴታ፤ እ.ኤ.አ በ2004 ከጆሴ ሞሪንሆ በመቀጠል የፕሪምየር ሊግ ዋንጫን ያነሳ ሁለተኛው ወጣት አሰልጣኝ ሆኗል።

በተጨማሪም እ.ኤ.አ በ1986 ኬኒ ዳልግሊሽ ከሊቨርፑል ጋር ባደረጉት ዓይነት በመጀመሪያው ዋና የአሰልጣኝነት ስራው ቡድኑን የሊጉ ሻምፒዮን ማድረግ ችሏል።
 
አርቴታ እ.ኤ.አ በታህሳስ 2019 ከተሾመ ጀምሮ አርሰናልን የቀየረ ሲሆን፤ አዲሱ ውሉም ያከናወናቸውን ስኬቶች የሚያንፀባርቅ እንደሚሆን ታውቋል።
 
የስፔናዊው አሰልጣኝ በነባር ኮንትራቱ በዓመት 10 ሚሊየን ፓውንድ ደመወዝ እና ለሻምፒዮንስ ሊግ በሚያልፍበት ወቅት የ5 ሚሊየን ፓውንድ ጉርሻ ያካተተ ክፍያንእንደሚያገኝ አይነገራል።

አዲሱ የደመወዝ ጭማሪ ግን የአትሌቲኮ ማድሪዱን አሰልጣኝ ዲዬጎ ሲሚዮኔን ገቢ ሊጠጋ እንደሚችል ዘጋርዲያን አስነብቧል።
 
 ሲሚዮኔ በዓመት 30 ሚሊየን ዩሮ (26 ሚሊየን ፓውንድ) በማግኘት የዓለማችን ከፍተኛ ተከፋይ አሰልጣኝ እንደሆኑ ይነገራል።

ፔፕ ጋርዲዮላ ደግሞ ከማንቸስተር ሲቲ 20 ሚሊየን ፓውንድ ይከፈላቸዋል።

ፔፕ ጋርዲዮላ የእሁዱን የመጨረሻ የሊግ ጨዋታ ተከትሎ ከኃላፊነታቸው ሲለቁ አርቴታ በእንግሊዝ አራቱ ከፍተኛ ሊጎች ውስጥ ረጅም ጊዜ ያገለገለ አሰልጣኝ ይሆናል።
 
አርሰናልን ለዋንጫ ያበቃ ስምንተኛው እና ከ2004ቱ አርሰን ቬንገር በኋላ የመጀመሪያው አሰልጣኝ የሆነው አርቴታ፣ ከሚቀጥለው የሻምፒዮንስ ሊግ የፍፃሜ ጨዋታ (ከፓሪስ ሴንት ዠርሜን) በኋላ የኮንትራት ድርድሩን እንደሚቀጥል ተገልጿል።
 
አርቴታ ከስፖርት ዳይሬክተሩ አንድሪያ ቤርታ ጋር በመሆን በተጫዋቾች ዝውውር እቅድ ላይ በንቃት እየተሳተፈ ይገኛል።

የክለቡ ተባባሪ ሊቀመናብርት ስታን እና ጆሽ ክሮንኬ ሰኞ ዕለት ከበርንሌይ ጋር በነበረው ጨዋታ የመዝጊያ ፕሮግራም ላይ “የውድድር ዘመኑ ሲያልቅ ዝም ብለን አንቀመጥም” ሲሉ ቃል ገብተዋል።

ክለቡ ባለፈው ክረምት እንዳወጣው 250 ሚሊየን ፓውንድ ባይሆንም፤ እ.ኤ.አ በ2023 ዴክላን ራይስን በ105 ሚሊየን ፓውንድ ያስፈረመበትን ዓይነት ታላቅ ዝውውር  ለማድረግ የሚያስችል በጀት መመደቡ ታውቋል።

ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ