የአረንጓዴ አሻራ ልማት ለመጪዉ ትውልድ ዋስትና በመሆኑ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች በንቃት መሳተፍ አለባቸዉ – አቶ ዘይኑ ሻዉዲን

የአረንጓዴ አሻራ ልማት ለመጪዉ ትውልድ ዋስትና በመሆኑ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች በንቃት መሳተፍ አለባቸዉ – አቶ ዘይኑ ሻዉዲን

ሀዋሳ፡ ሐምሌ 10/2015 ዓ.ም (ደሬቴድ) የአረንጓዴ አሻራ ልማት ለመጪዉ ትውልድ ዋስትና በመሆኑ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች በንቃት መሳተፍ እንዳለባቸዉ በጉራጌ ዞን የቀቤና ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዘይኑ ሻዉዲን ተናግረዋል።

በወረዳዉ “ነገን ዛሬ እንትከል” በሚል መሪ ቃል የችግኝ ተከላ መርሃግብር በወረዳዉ ሱንካ ቀበሌ ተከናውኗል።

በመርሃግብሩ ላይ የተገኙት የጉራጌ ዞን ፐብሊክ ሰርቪስና ሰዉ ሀብት ልማት መምሪያ ሀላፊ አቶ አብደላ ጀማል ባስተላለፉት መልዕክት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፋ የመጣው የሙቀት መጠን መጨመር አለም ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያደረሰ መምጣቱን ተክትሎ ችግሩን ለመቋቋም አረንጓዴ ልማት ላይ ትኩረት መስጠት እንደሚገባ ገልፀዋል።

የቀቤና ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዘይኑ ሻውዲን እንደተናገሩት የአረንጓዴ አሻራ ልማት ለመጪዉ ትውልድ ዋስትና በመሆኑ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች በችግኝ ተከላ መርሃግብር በንቃት በመሳተፍ የበኩላቸዉን መወጣት አለባቸው።

ችግኞችን መትከል ነፋሻማ አካባቢን ከመፍጠር በተጨማሪ የሀገር ዕድገት መሰረት ነዉ ያሉት ዋና አስተዳዳሪዉ በመሆኑም ህብረተሰቡ ችግኞችን መትከልና መንከባከብ እንዳለበት አቶ ዘይኑ ተናግረዋል።

የወረዳው ምክትል አስተዳዳሪና የወረዳው ግብርና ፅ/ቤት ሀላፊ አቶ አብድልሽኩር ደሊል በበኩላቸው ሁለተኛው ምዕራፍ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር አካል የሆነው የአንድ ጀምበር የ500 ሚሊዮን የችግኝ ተከላ መርሃግብር በወረዳው 2 ሚሊየን ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ ወደ ተግባር ተገብቷል ብለዋል። 

በተያዘዉ የክረምት ወራት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸዉ የተለያዩ ችግኞችን ለመትከል እቅድ ተይዞ እየተሰራ እንደሚገኝ ገልፀው ህብረተሰቡ ችግኞችን መትከል ላይ ብቻ ሳይሆን እንዲፀድቁ ሀላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ ተናግረዋል።

አርሶ አደር ግዛዉ መሀመድ፣ ኑር ጀማል ሰማንና ወይዘሮ መሁባ መሀመድ ከመርሃ ግብሩ ተሳታፊዎች መካከል ይገኙበታል። በሰጡት አስተያየት በቀበሌያቸዉ በአረንጓዴ ልማት አሻራ ባለፉት አመታት የተሻለ ዉጤት እንዳገኙና የአርሶ አደሩ ምርትና ምርታማነት እየጨመረ መምጣቱን ተናግረዋል። በቀጣይ የተተከሉ ችግኞች እንዲፀድቁ ሀላፊነታቸዉን እንደሚወጡም አስተያየት ሰጪዎቹ ገልፀዋል።

በመርሃግብሩ ላይ ከዞን እና ከወረዳ የተውጣጡ አመራሮች እንዲሁም የአካባቢው ነዋሪዎችና የፀጥታ አካላት ተሳትፈዋል።

ዘጋቢ፡ ሪያድ ሙህዲን – ወልቂጤ ጣቢያችን