በህገ-ወጥ መንገድ ከሀገር ሊወጣ የነበረ የውጭ ሀገር ገንዘብ እና አደገኛ ዕፅ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ተያዘ

በህገ-ወጥ መንገድ ከሀገር ሊወጣ የነበረ የውጭ ሀገር ገንዘብ እና አደገኛ ዕፅ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ተያዘ

ሀዋሳ፡ ሐምሌ 03/2015 ዓ.ም (ደሬቴድ) በህገ-ወጥ መንገድ ከሀገር ሊወጣ የነበረ የውጭ ሀገር ገንዘብና አደገኛ ዕጽ በአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ መያዙን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ገለፀ።

መነሻውን አዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ አድርጎ በሕገ-ወጥ መንገድ ወደ ዱባይ ሊወጣ የነበረ 44 ሺህ 440 ዩሮ፣ 11ሺህ 850 የአሜሪካን ዶላር፣ 20 ሺህ 480 ፖውንድ (GBP)፣ 3ሺህ 700 ዲርሃም፣ 3መቶ የሲዊዝ ፍራንክ እና 1ሺህ 700 የሳውዲ ሪያል የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ፣ የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት፣ የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን እና የአየር መንገድ የሴኩሪቲ ሠራተኞች ባደረጉት ጠንካራ ፍተሻ በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ከውጭ ሀገር ተጠርጣሪዎች ጋር መያዛቸውን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ መረጃ ያመለክታል።

በተመሳሳይ መነሻውን ብራዚል ሳኦፖሎ አድርጎ በአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ በኩል ወደ ሌሎች ሀገሮች ሊተላለፍ የነበረ በዱቄት መልክ የተዘጋጀ 17.90 ኪሎ ግራም ኮኬይን አደገኛ ዕፅ የፀጥታ አካላቱ ባደረጉት ጠንካራ ፍተሻ ከሦስት የውጭ ሀገር ዜጎች ጋር በቁጥጥር ሥር ውሎ ምርመራ እየተጣራ መሆኑን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አክሎ ገልጿል።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በመሰል የወንጀል ድርጊቶች የተሰማሩ ግለሰቦችና ቡድኖች በየትኛውም መንገድ ማምለጥ እንዳይችሉ የፀጥታ አካላቱ እየወሰዱ ያሉትን ህጋዊ እርምጃ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አሳስቧል።