የአረጋውያንን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማሳደግ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ድጋፍ ወሳኝ ነው

የአረጋውያንን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማሳደግ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ድጋፍ ወሳኝ ነው

ሀዋሳ፡ ሐምሌ 04/2015 ዓ.ም (ደሬቴድ) የሀገር ባለውለታ የሆኑ የአረጋውያንን ተሳትፎ እና ተጠቃሚነትን ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት የሁሉም ባለድርሻ አካላት ድጋፍና ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን የወልቂጤ ከተማ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ጽ/ቤት ገለፀ።

ጽህፈት ቤቱ የወልቂጤ ከተማ እና አካባቢው አረጋውያን ማህበር የ2015 በጀት ዓመት የስራ አፈፃፀም ማጠቃለያ ጉባኤ ባካሄደበት ወቅት ነው።

በጉባኤው ላይ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት በወልቂጤ ከተማ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ጽ/ቤት የማህበራዊ ደህንነት ልማት አስተባባሪ ወ/ሮ ፈትያ በደዊ እንዳሉት የሃገር ባለውለታ የሆኑት አረጋውያንን በመደገፍ አቅማቸውን ማጎልበት ያስፈልጋል ብለዋል።

የአረጋውያን ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት ማሳደግ እንዲቻልም የመንግስት እና የሌሎች ባለድርሻ አካላት ድጋፍና ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ገልፀዋል።

የወልቂጤ ከተማ እና አካባቢው አረጋውያን ማህበር ሊቀመንበር አቶ ይርጋለም በርሄ ባቀረቡት ሪፖርት የማህበሩን አባላት ተሳትፎ እየቀነሰ መምጣቱን አንስተው ጧሪ ቀባሪ ለሌላቸው አረጋውያን ከተለያዩ አካላት ጋር በመሆን ድጋፍ እና ክትትል እየተደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

አቶ ይርጋለም አክለውም አባላቱን አደራጅቶ የተሻለ ውጤት ለማምጣት እንዲቻል እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን ማጠናከር እና ያባላቱን ውጤታማነት በተገቢው ለማረጋገጥ የግብአት እና የመስረያ ቦታ እጥረት እንዲቀረፍላቸው ጠይቀዋል።

በወልቂጤ ከተማ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ጽ/ቤት የማህበራዊ ደህንነት ልማት አስተባባሪ ወ/ሮ ፈትያ በደዊ የማህበሩ ጥያቄ ደረጃ በደረጃ ምላሽ እንዲያገኝ ከባለድርሻ አካላት ጋር እንደሚሰራ አስረድተዋል ።

የጉባኤው ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያያትም የኢኮኖሚ ተሳትፎ የማሳደግ ስራ መስራት የሚቻለው የተቀረፁ ፕሮጀክቶች ስራ ላይ ሲውሉ ነው ብለዋል።

የማህበሩ አዋጅ እና ደንቦችን ማሻሻል እና ቢዝነስ ፕላኑ ለማሳደግ የሚመለከታቸው አካላት በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባም የጉባኤ ተሳታፊ አረጋውያን ጠቁመዋል ።

ዘጋቢ:  እርካብነሽ ወ/ማርቆስ- ከወልቂጤ ጣቢያችን