በህብረተሰቡ የሚከናወኑ የልማት ስራዎች ጥራትን ያሟሉ በመሆናቸው ብዙ ልምድ ተወስዶባቸዋል – ምክትል ርእሰ መስተዳደር ዶክተር እንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ

በህብረተሰቡ የሚከናወኑ የልማት ስራዎች ጥራትን ያሟሉ በመሆናቸው ብዙ ልምድ ተወስዶባቸዋል – ምክትል ርእሰ መስተዳደር ዶክተር እንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ

ሀዋሳ፡ ሐምሌ 03/2015 ዓ.ም (ደሬቴድ) በህብረተሰቡ የሚከናወኑ የልማት ስራዎች ጊዜ ገንዘብ ጥራትን ያሟሉ በመሆናቸው በተግባሩ ብዙ ልምድ ተወስዶባቸዋል ሲሉ የደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳደር ዶክተር እንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ ተናገሩ።

በቤንች ሸኮ ዞን በደቡብ ቤንች ወረዳ 27 ሚሊየን ብር በሚጠጋ ወጪ ተገንብተው ለአገልግሎት የበቁት የድልድይ ግንባታዎችም በክልሉ እና በዞኑ ከፍተኛ አመራሮች ተጎብኝተዋል።

አቶ መራዊ መኮንን እና አቶ አዘዘ ጸሀይ በደቡብ ቤንች ወረዳ የደብረወርቅ ከተማ ነዋሪዎች ናቸው።

በወረዳው የሚኖሩ ነዋሪዎች ፈተና የሆነባቸውን እና ምርታቸውን እንኳ ወደገበያ ለማውጣት ፈተና የሆነባቸው በአካባቢያቸው ያሉ ወንዞች ድልድይ አለመኖር እንደነበር ያወሳሉ።

ነዋሪዎቹ ቀደም ሲል ድልድይ በወረዳ እና በዞን አስተዳደር ማሰራት ስለማይቻል የክልሉን እገዛ ሲጠብቁ መቆየታቸውን ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ እስከመቼ ከላይ እንጠብቃለን ብለው የወረዳውን ህዝብ አሰባስበው በተለያዩ ጊዜ ፈተና የሆነባቸውን ሶስት ድልድዮችን በራሳቸው በህብረተሰቡ ተሳትፎ 27 ሚሊየን ብር በሚጠጋ ወጪ መስራታቸውን እና ለአገልግሎት ማብቃታቸውንም ተናግረዋል።

ነዋሪዎቹ በድልድይ ግንባታ ያገኙትን ልምድ ተጠቅመው በየቦታው የሚታዩ የመንገድ ችግሮችን ለመፍታት እና የቃቂ ወንዝን ለመስራትም ግሬደር እና ገልባጭ መኪናዎችን ለመግዛት በዝግጅት ላይ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

የደቡብ ቤንች ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ወልዱ ባጪ በበኩላቸው በመንግስት ብቻ ይሰሩ የነበሩት የድልድይ ስራዎችን በህብረተሰቡ መስራት እንደሚቻል እና የወረዳውም ህዝብ ባደረገው ርብርብ ሶስት ድልድዮችን በመስራት ለአገልግሎት ማብቃት መቻላቸውን ተናግረዋል።

ነዋሪዎቹ በቀጣይም አሁን ያለውን ህዝባዊ መነቃነቅ በማስቀጠል በወረዳው ያለውን የመንገድ ችግር ለመቅረፍ ሰላሳ ሚሊየን ብር በማሰባሰብ የተለያዩ ማሽነሪዎችን ለመግዛት ግብ ጥለው በመንቀሳቀስ ላይ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

የቤንች ሸኮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ቀበሌ መንገሻ በበኩላቸው በመንግስት ከሚሰሩ የልማት ስራዎች ባለፈም በህብረተሰቡ ተሳትፎ የሚሰሩ የልማት ስራዎች በዞኑ ከጊዜ ወደጊዜ እያደጉ መምጣታቸውን ጠቁመዋል።

ለዚህም አንደ ማሳያ የሚሆኑት በደቡብ ቤንች ወረዳ በህብረተሰቡ ተሳትፎ ተገንብተው ለአገልግሎት የበቁት የድልድይ ግንባታዎች ሲሆኑ ህብረተሰቡ ከተባበረ ማንኛውንም ስራ መስራት እንደሚችል ማሳያ መሆኑን አንስተዋል።

በደቡብ ቤንች የተጀመረው የህብረተሰብ የንቅናቄ ስራዎች በሌሎች ወረዳዎች መቀጠል መቻላቸውንም ተናግረዋል።

የደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳደር ዶክተር እንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ በበኩላቸው በክልሉ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ በርካታ የልማት ተግባራት እየተከናወኑ ቢሆንም ከህዝቡ የልማት ፍላጎት አንጻር በመንግስት በተፈለገው ልክ ለመተግበር የበጀት ውስንነት መኖሩን ተናግረዋል።

ይህን ችግር ለመቅረፍም በክልሉ ባሉ ሁሉም ዞኖች ህብረተሰቡን በማነቃነቅ የመንገድ የውሃ እና ተመሳሳይ የልማት ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ተናግረዋል። በቤንች ሸኮ ዞን በደቡብ ቤንች ወረዳ በህብረተሰብ ተሳትፎ ሶስት ድልድዮች ተገንብተው ለአገልግሎት በቅተዋልም ብለዋል።

እነዚህ ድልድዮች ሲገነቡ በውስን ሀብት በአጭር ጊዜ እንዲሁም በተገቢው ጥራት የተገነቡ መሆናቸውን መመልከት መቻላቸውን ጠቁመዋል።

በጉብኝቱም የክልሉ እና የዞኑ ከፍተኛ አመራሮች ተሳታፊም ሆነዋል።

ዘጋቢ: አብዮት በቀለ – ከሚዛን ጣቢያችን