ከ1 ነጥብ 8 ቢሊየን በላይ ሀብት ላስመዘገቡ እና ከ5 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል ለፈጠሩ 377 ኢንተርፕራይዞች እውቅና ተሰጠ

60 የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ጠቢያዎች፣ 60 የዘርፉ ምርጥ ፈጸሚዎች፣ 100 ወደ ታዳጊ መካከለኛ የተሸጋገሩ ኢንተርፕራይዞች፣ 50 ሞዴል ኢንተርፕራይዞች እንዲሁም የቴክኒክና ሙያ ተቋማት የእውቅናው አካል ናቸው።

እውቅናና ሽልማቱን ያበረከቱት የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን  በራሳቸው ጥረት በመንግሥት በሚደረጉ ድጋፎች በመታገዝ ወደ ለውጥ የተሸጋገሩ ኢንተርፕራይዞችን እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።

የሥራ ዕድል ተጠቃሚነትን በበቂ ክህሎት በማስደገፍ ለማስፋፋት በኢትዮጵያ የተጀመሩ  እሳቤዎች አህጉራዊ ይዘት እንዲኖራቸው መደረጉን ያስታወቁት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ  በሂደትም አለም አቀፋዊ ይዘት እንዲኖረው ይሰራል ብለዋል።

በአፍሪካ ካለው ከ1 ነጥብ 4 ቢሊዮን የህዝብ ቁጥር ውስጥ 60 በመቶ ወጣት ትውልድ እንደሆነም አስታውቀዋል።

ለዚህ ለሰፊው  አምራች የሰው ኃይል የሥራ ዕድል ማመቻቸትና መፍጠር አሁን ላይ ትልቁ የአፍሪካ አህጉር ወቅታዊ አጀንደ ሆኖ ይገኛል ሲሉም አቶ ደመቀ ተናግረዋል።

ስለሆነም ከተሠራው ይልቅ ያልተሠራው ስለሚበልጥ ለላቀ ስኬት መስራትና መጓዝ  እንደሚገባም አስገዝበዋል።

የሥራና ክህሎት ሚኒስትር  ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል በበኩላቸው  ከሰኔ 30 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ከአፍሪካ ህብረት እና ከአፍሪካ ኤሌክትሮኒክስ ትሬድ ግሩፕ ጋር በመተባበር የተካሄደው የአፍሪካ የሥራ ዕድል ፈጠራ ፎረም በስኬት መጠናቀቁን ተናግረዋል።

በአፍሪካ ብሎም በኢትዮጵያ ብቁ የሆነ የክህሎት ሥልጠና አለመኖር ለሥራ አጥነት ችግር መንሰራፋት ከፍተኛ ተግዳሮት ሆኖ ቆይቷል ያሉት ወ/ሮ ሙፈሪህት አፍሪካዊ የትብብር ማዕቀፍ መፍጠር ከተቻለ ችግሩን መፍታት ይቻላል ብለዋል።

አፍሪካውያን ለአፍሪካውያን በሚል እሳቤ የ Royal Kingdom Assembly Secretariat የ8 ቢሊዮን ዶላር ሀብት ለኢትዮጵያ የሥራ ዕድል ፈጠራ ድጋፍ ለማድረግ ቃል መግባቱንም  ሚኒስትሯ አስታውቀዋል።

ለምርጥ ፈጻሚ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ሰጪዎች የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የትምህርት ዕድል  እንደሚያመቻችም ወ/ሮ ሙፈሪሃት አረጋግጠዋል።

 ዘጋቢ፡  ጌታሁን አንጭሶ