የሞዴል አርሶ አደሮችን ተሞክሮ በማስፋት ዘርፉን ለማሳደግ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባም ተመላክቷል።
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የጠምባሮ ልዩ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ወ/የሱስ መኮንን፤ መንግስት በግብርና ዘርፍ የአርሶ አደሩን የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ እንዲቻል ዘርፈ ብዙ ጥረቶችን እያደረገ እንደሚገኝ ጠቁመው በልዩ ወረዳው የግምባር ቀደም አርሶ አደሮችን ተሞክሮ ለማስፋት በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
እንደ ልዩ ወረዳው ከ4 ሺ 5 መቶ በላይ ሄክታር ማሳ የቅመማ ቅመም ምርት በሆነው በዝንጅብል ለመሸፈን የታቀደ ሲሆን 160 ኩንታል በሄክታር እንደሚጠበቅም ገልፀዋል።
አርሶ አደሩ ወጪ ቆጣቢ የሆነውን ኮምፖስት በመጠቀም የተለያዩ የግብርና ምርቶችን በማልማትና በተለያዩ የሌማት ትሩፋት ተግባራት በመሳተፍ የሚያከናውናቸው ተግባራት የሚበረታቱ መሆናቸውን የገለፁት ኃላፊው፤ እንደ ልዩ ወረዳው በአጠቃላይ በዝንጅብል ብቻ ከ1 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ አመላክተዋል።
ገራድ ተስፋዬ ለንኬቦ በጠምባሮ ልዩ ወረዳ የሶያሜ ቀበሌ አርሶ አደር ሲሆኑ ከ2 ሺ በላይ ከብቶችን ከማስቆጠር ባለፈ በ60 ሄክታር መሬት የተለያዩ የግብርና ልማት ስራዎችን በመስራት ድህነትን ማሸነፍ የቻሉ ታታሪ አርሶ አደር ናቸው።
በዘንድሮ የመኸር እርሻ ወቅትም ከዝንጅብል ብቻ ከ60 ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠብቁ ገልፀዋል።
50 ጥማድ በሬዎችን ለእርሻ ተግባር እንደሚጠቀሙ የገለፁት አርሶ አደር ገራድ ተስፋዬ፤ በተለያዩ የስራ መስኮች ከ200 በላይ ለሚሆኑ ሰዎች የስራ እድል እንደፈጠሩላቸው ተናግረዋል።
በጠምባሮ ልዩ ወረዳ የሶያሜ ቀበሌ ግብርና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ታደለ ለንገና፤ አርሶ አደሩ ከዘመናዊ ግብርና ልማት ጋር የተዋሀዱ ለሌሎች አርሶ አደሮች ምሳሌ የሚሆኑ ስለመሆናቸው በመግለጽ እንደነ ገራድ ተስፋዬ ያሉ አርሶ አደሮችን በማፍራት የግብርናውን ክፍለ ኢኮኖሚ ለማሳደግ የድርሻቸውን እየተወጡ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
የልዩ ወረዳውና የሙዱላ ከተማ አስተዳደር አመራር አካላት የሞዴል አርሶ አደሮችን ማሳ ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።
ዘጋቢ: አማኑኤል አጤቦ – ከሆሳዕና ጣቢያችን

More Stories
የማታ 1፡00 ዜና 24፤ ሀዋሳ፡ ሕዳር 17/2018 ዓ.ም
የቀን 6፡00 ዜና 24፤ ሀዋሳ፡ ህዳር 16/2018 ዓ.ም
የማታ 1፡00 ዜና 24፤ ሀዋሳ፡ ህዳር 15/2018 ዓ.ም