“አካል ጉዳተኝነት ማንነት ነው” – አቶ መሀመድ ሸይቾ

በገነት ደጉ

ድሮ ድሮ አካል ጉዳተኞች ቁጭ ብለው አጋዥ እንደሚጠብቁ ይታሰብ ነበር፡፡ አሁን አመለካከቱም ይሁን እሳቤው እየተሻሻለ መጥቷል፡፡

አካል ጉዳተኞችም በርካታ ለውጥ የሚያመጡ ስራዎችን በመስራት ከራሳቸው አልፈው ሀገራቸውንና ወገናቸውን ሲያግዙ ማየት እየተለመደ ነው፡፡

ከሰሞኑን ወደ ስልጤ ዞን ወራቤ ከተማ ተጉዘን የአንድ አካል ጉዳተኛ ተሞክሮ ልናስቃኛችሁ ወደድን፡፡ መልካም ንባብ፡፡

አቶ መሀመድ ሸይቾ ይባላሉ፡፡ በቅጽል ስማቸው “ማሜ ሞባይል እና ሶላር” በመባል ይታወቃሉ፡፡ በስልጤ ዞን ላንፉሮ ወረዳ ልዩ ስሙ ጦራ 01 ቀበሌ ነው የተወለዱት፡፡

የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ገና በልጅነት ዕድሜያቸው ነው፡፡ ወላጆቻቸው በፖሊዮ ምክንያት ለአካል ጉዳት እንደተዳረጉ ነግረዋቸዋል፡፡ ቤተሰቦቻቸው ባህላዊ ህክምናዎችን እንዲያገኙ ወደ ተለያዩ ቦታዎች ቢሄዱም መፍትሄ ማግኘት አልቻሉም፡፡

በሶስት ዓመታቸው የተሻለ የህክምና እርዳታ ለማግኘት ከቤተሰባቸውና የቅርብ ዘመዶቻቸው ጋር ወደ አዲስ አበባ ባቀኑበት፣ እድገታቸውን በዚያው አደረጉ፡፡

“በአዲስ አበባ የሚገኘውን ቸሻየር የአካል ጉዳተኞች ድርጅት ከልብ አመሰግናለሁ። ቀድሞ በሁለት እግሬና እጄ ነበር አጎንብሼ የምራመደው፡፡ ቸሻየር ማዕከል ውስጥ ገብቼ ነው ሙሉ ህክምና ተደርጎልኝ በክራንች ቆሜ መሄድ የቻልኩት” ሲሉ ተቋሙ ያደረገላቸውን ይናገራሉ፡፡

አዲስ አበባ ኮልፌ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ከ1ኛ እስከ 7ኛ ክፍል መከታተላቸውን የገለፁት አቶ መሀመድ፣ በድጋሚ ወደ ጦራ በመመለስ የ8ኛ እና የ9ኛ ክፍል ትምህርታቸውን ተከታትለዋል። ከዚያም ደግሞ ወዳደጉባት አዲስ አበባ በመሄድ የ10ኛ ክፍል ትምህርታቸውን አጠናቀዋል፡፡

በትምህርታቸው ጥሩ ዝንባሌ ያላቸው ተማሪ ቢሆኑም በወቅቱ የነበሩ ውጣ ወረዶች አሉታዊ ተፅዕኖ እንደፈጠረባቸው ያስታውሳሉ፡፡

ከትምህርቱ ጎን ለጎን ራሳቸውን ለመርዳት የሊስትሮ ስራ ሰርተዋል፡፡ በዚህም ፍላጎትና ዝንባሌያቸው ንግዱ ላይ ሆነ፡፡

“ከሊስትሮ ስራዬ ከፍ ስል መርካቶ ላይ አንዳንድ ንግድ ስራዎች እሰራ ነበር፡፡ የንግድ ስራው እያደገልኝ ሲመጣ መርካቶ ይርጋ ሀይሌ አካባቢ ተከራይቼ መነገድ ጀመርኩኝ” ሲሉ ንግድ የጀመሩበትን አጋጣሚ ያስታውሳሉ፡፡

ይሁን እንጂ ለንግዱ የተከራዩት ከአቅማቸው ጋር አልተመጣጠነም፡፡ በዚህም ከራሳቸው ጋር መክረው ወደ ትውልድ አካባቢያቸው ላንፉሮ ወረዳ ጦራ ተመለሱ፡፡

በወቅቱም በአካባቢው ብዙ ያልተለመደ በመሆኑ የኤሌትሮኒክስ ዕቃዎችን በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ ተጠቃሚ መሆን ቻሉ፡፡ ለታናናሽ ወንድሞቻቸው የስራ ዕድል በመፍጠር የስራ አድማሱን ማስፋት ቻሉ፡፡

ከኤሌክትሮኒክስ ንግዱ በተጨማሪ የወንዶች ፀጉር ቤት ከፈቱ፡፡ ይሁን እንጂ በዚህ ስራ አልዘለቁም፡፡ ሁለቱንም ስራዎች ማስኬድ ከገንዘብም ከጊዜም አንፃር ሲከብድባቸው ፀጉር ቤቱን እስከነእቃዎቹ አከራይተው የኤሌትሮኒክስ ስራው ላይ ብቻ ትኩረት አደረጉ፡፡

“ለእኔ አካል ጉዳተኛ መሆን ምንም ማለት አይደለም፡፡ አካል ጉዳተኛ መሆን ከማንኛውም የስኬት ጎዳና አላገደኝም፡፡ ማንኛውም ሰው መስራት የሚችለውን ስራ መስራት እችላለሁ፡፡ መንፈሰ ጠንካራ በመሆኔ እጅግ ደስተኛ ነኝ፡፡

“ለብዙ አካል ጉዳተኞች አርአያ ነኝ ብዬ አስባለሁ፡፡ ዋናው ቁም ነገር እራስን አሳምኖ መገኘትና ጉዳት ለደረሰበት አካል መፍትሄ መፈለግ ነው የሚል ጽኑ እምነት አለኝ፡፡” በማለት ለስኬት የበቁበትን ምስጢር ያጋራሉ።

በስራው ውጤታማ በመሆናቸው በወረዳው በኤሌክትሮኒክስ ስራ ቅርንጫፎችን ማስፋፋት ችለዋል፡፡ ከላንፉሮ ወረዳ ባለፈ ቀስ በቀስ ሚቶ ወረዳ ላይ ቁጥር 1 እና 2 የኤሌትሮኒክስ ዕቃዎች መሸጫ ሱቆችን ከፍተዋል፡፡ ወራቤ ላይ በተመሳሳይ ቁጥር 4 የኤሌክትሮኒክስና የሶላር ሱቅ ከፍተዋል፡፡

ስራቸውን ያስፋፉበትንም መንገድ ሲገልጹ፡-

“ከኦሞ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም ጋር በመተባበር ሶላር ለአካባቢው አርሶ አደር ከወለድ ነፃ በብድር ማከፋፈል ጀመርኩ፡፡ አርሶ አደሩም ምርቱን ሲሰበስብ ክፍያውን ይፈጽማል፡፡ በዚህም እጅግ ውጤታማ ነኝ፡፡

“አብረውኝ የሚሰሩ እና የሚያበረታቱኝ ማዕድንና ኢነርጂ፣ ኦሞ ማይክሮ ፋይናንስ፣ ሴቶችና ህፃናት፣ እንዲሁም የአካባቢ ጥበቃ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እያደረጉ ነው፡፡ ከነዚህም ጋር ለአርሶ አደሩ ህጋዊ የሆኑ ሶላሮች እንዲቀርቡ የማድረጉን ስራዎች በስፋት በዞኑ ባሉ ወረዳዎች ውክልና በመውሰድ እያቀረብኩ እገኛለሁ፡፡

“አካል ጉዳተኛ ማለት በእኔ እሳቤ መልከ ብዙ ነው፡፡ ለእኔ አካል ጉዳተኝነት ማንነት ነው፡፡ ያንን ማንነት ይዞ ውጤት ማምጣት የምትችልበትን መንገድ ቀይሶ የተፈለገውን ውጤት ማምጣት ይቻላል የሚል እምነት አለኝ” ነው ያሉት፡፡

“ያለብኝን ጉዳት ተቀብዬ ችግርን ላሸንፍ የምችልበትን መንገድ ቀይሼ እራሴንና ቤተሰቦቼን ለመደገፍ የሚያስችለኝን እንቅስቃሴ ማድረግ እንዳለብኝ አምን ነበር፡፡ ይህንን እሳቤ ወደ ተግባር በመለወጤ ዛሬዬን ጥሩና ብሩህ አድርጌያለሁ፡፡” በማለትም አክለዋል፡፡

ሰዎች ከራሳቸው ማንነት ጋር ሊሄድ የማይችሉ ስራዎችን መጀመር እንደሌለባቸውም ይመክራሉ፡፡

አካል ጉዳተኛ መሆናቸው ቤተሰብ ከመመስረትና ወልዶ ከመሳም አላገዳቸውም። ባለትዳርና የአራት ወንድ ልጆች አባት ናቸው። ብዙ ጊዜ “ከጠንካራ ወንድ ጀርባ ጠንካራ ሴቶች አሉ” የሚለው አባባል ባለቤታቸውን እንደሚገልጽም ነው የተናገሩት፡፡

ቀደም ሲል ከወላጅ እናታቸው፣ ከወንድሞቻቸው ብሎም ከሚቀርቡት ሰዎች የሚያገኙትን ድጋፍ በሙሉ ዛሬ ከባለቤታቸው ያገኛሉ፡፡ በስኬታቸው ሁሉ የባለቤታቸው ሚና ትልቅ እንደሆነም ይገልጻሉ፡፡

“የወደፊት እቅድዎ ምንድነው?” ብለን ላነሳንላቸው ጥያቄ ምላሻቸውን እንዲህ ሲሉ ነበር ያጋሩን፡፡

“ሁሉም ሰው የራሱ ምኞት አለው” በማለት ነው አቶ መሀመድ የጀመሩት፡፡ የአካል ጉዳተኞችን ለመርዳት የሚያስችል ተቋም ለመገንባት ዕቅድ አላቸው፡፡ በየቦታው ያሉ የአካል ጉዳተኞችና አቅመ ደካሞችን ችግሮቻቸውን ማቃለል ነው ህልምና ምኞታቸው፡፡ በስራ አጋጣሚ ወደ አርሶ አደሩ መንደር ይንቀሳቀሳሉ፡፡ በዚህም የተመለከቱት አሳዛኝ ነገር ለአንድ በጎ ነገር አነሳሳቸው፡፡

አካል ጉዳተኞች በየስርቻው እና በየቤቱ ተዘግቶባቸው እንዲሁም እንደ እንስሳት ታስረው ምግብ ተሰጥቶአቸው እዚያው የሚፀዳዱ በርካቶች እንዳሉም ተመለከቱ፡፡

“የሰው ልጆችን ችግር ነቅሰን በማውጣት የምናግዝበት እና ከህብረተሰቡ የተገለሉትን አካል ጉዳተኞች ከሰዎች ጋር የሚቀላቀሉበትን ማዕከላት መገንባት ነው የምፈልገው፤ ይህም ልቤንና አዕምሮዬን የሚያሳርፈኝ ሆኖ በማግኘቴ ነው ዓላማ አድርጌ የሰነቅኩት” ይላሉ፡፡

አክለውም፡-

“ገዝቶ ከመሸጥ ባለፈ ጎን ለጎን አሁን የጀመርኩትን የኤሌክትሮኒክስ ንግድ ወደ ላቀ ደረጃ ማድረስ እፈልጋለሁ፡፡ በዚህም የአካባቢውን ህብረተሰብ ብሎም ሀገሬን ተጠቃሚ ሊያደርግ የሚችል ፋብሪካ መትከል ዘላቂ መፍትሄ ነው የሚል አስተሳሰብ በውስጤ አለ፡፡ ይህም የእቅዴ አካል ነው፡፡

“ይህንንም ራዕይ በአጭር ጊዜ ውስጥ አሳካለሁ ብዬ አስባለሁ፡፡ ጅምር ስራዎችም አሉኝ፡፡ በሀሳብ ደረጃ የያዝናቸው አንድ ሁለት ፕሮጀክቶች አልቀው ወደ ስራ ለመግባት ጥቂት ጊዜ የቀራቸው አሉ፡፡

“የቅመማ ቅመም ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ለማቋቋም የተወሰነ ሂደት ተጉዘናል፡፡ ቀሪ ጥቂት ስራዎች ይቀራሉ፡፡ ሌላው ደግሞ ከብት እርባታና ከብት ማድለብ ጋር ተያይዞ በምንኖርበት አካባቢ የወተት አቅርቦት መሰረታዊ ችግር ነውና የተጀመሩ ስራዎችን በቅርብ ቀን ለማሳካት ደፋ ቀና እያልን ነው። በቅርቡ ይዘን ብቅ እንላለን የሚል ተስፋ አለኝ፡፡” ሲሉ ነው አቶ መሀመድ የተናገሩት፡፡