የፌደሬሽን ምክር ቤት እና ተጠሪ ተቋማት በካፋ ዞን ሺሺንዳ ከተማ አስተዳደር ለአቅመ-ደካሞች ያስገነቧቸውን መኖሪያ ቤቶች እያስረከቡ ነው
በከተማው አምስት መኖሪያ ቤቶች ከነሙሉ እቃዎቻቸው ተገንብተው በዝቅተኛ የኢኮኖሚ ሁኔታ ላይ ለሚገኙ ቤተሰቦች የተላለፉ ሲሆን፤ ለቤት መግቢያ የሚሆን የእህልና የበግ ሙክት ስጦታ ለቤተሰቦቹ ተበርክቷል።
የሺሺንዳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሀብታሙ ገብረኢየሱስ በ90 ቀናት ውስጥ አምስት ቤቶችን ገንብቶ በማጠናቀቅ ያስረከቡትን የፌደሬሽን ምክር ቤት እና ተጠሪ ተቋማት አመስግነዋል።
ቤቶቹ በ5 ሚሊዬን ብር ተገንብተው መጠናቀቃቸውን አስታውቀው፥ ወቅቱ ሺሺንዳ ከተማን የማልማት ስራ እየተሰራ ያለበት በመሆኑ እነኚህ ቤቶች የከተማውን ውበት ጨምረዋል ብለዋል።
በአምስቱ ቤተሰቦች እና በከተማ አስተዳደሩ ደስታ የተፈጠረበት ተግባር መሆኑን በመግለፅ ፤ የመደጋገፍ ባህልን ማስቀጠል ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።
የካፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳሻው ከበደ በበኩላቸው ፤ የብልፅግና አስተሳሰብ በሆነው የመደመር እሳቤ መደጋገፍ ባህል እየሆነ መጥቷል ብለዋል።
የፌደሬሽን ምክር ቤት የሚሰራቸው ተግባራት በአርዓያነት የሚታይና ፋይዳው የጎላ መሆኑን ጠቅሰው ፤ ከ230 ሺህ በላይ በጎ ፈቃደኞች በካፋ ዞን ደረጃ በክረምት ወራት በጎ ፈቃድ ስራዎችን መስራታቸውንም አውስተዋል።
የፌደሬሽን ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ትግሉ መለሠ በምክር ቤቱ የሚከናወኑ በጎ ተግባራት እንደ ሀገር ለዜጎች ምቹ ሀገር የመፍጠር እሳቤ አንዱ አካል መሆኑን ተናግረዋል።
በአጭር ጊዜ ውስጥ ለተቸገሩ ወገኖች ቤቶች ተሰርተው የተጠናቀቁበት ሁኔታ ፕሮጀክቶችን ጀምሮ በተያዘላቸው ጊዜ የመጨረሱ ሁኔታ እያደገ መምጣቱን ያሳያል ብለዋል።
ቤት የተሰራላቸው ነዋሪዎች መካከል ወይዘሮ እታገኝ ወልደገብርኤል፣ ወይዘሮ አበበች አስፋው፣ አቶ ለገሰ ቀነዓ እና ሌሎችም በሰጡት አስተያየት ይህ ተግባር በህይታቸው ላይ ትልቅ ለውጥ የፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል።
ስለተደረገላቸው መልካም ተግባርም ሁሉንም አካላት አመስግነዋል።
በርክክብ መርሐ-ግብሩ ላይ የፌደሬሽን ምክር ቤትና የተጠሪ ተቋማት ኃላፊዎች፣ የዞኑ ብልፅግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አጥናፉ ኃይሌ፣ የሀገር ሽማግሌዎችና የአካባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል።
ዘጋቢ፡ ዮሐንስ ክፍሌ – ከቦንጋ ጣቢያችን
More Stories
ግራሃም ፖተር የሲዊዲን ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ በመሆን ተሾሙ
የወባ በሽታ ስርጭትን በዘላቂነት መቀነስ እንዲቻል በትኩረት እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ
የክረምት በጎ ፈቃድ አንድ አካል የሆነው የቡርጂ ዞን ሶያማ ከተማ አስተዳደር ሲካሄድ የሰነበተው የእግር ኳስ ሻምፒዮና የማጠቃለያ መርሃ-ግብር ተካሂዷል