የወባ በሽታ ስርጭትን በዘላቂነት መቀነስ እንዲቻል በትኩረት እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

የወባ በሽታ ስርጭትን በዘላቂነት መቀነስ እንዲቻል በትኩረት እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ ጥቅምት 10/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) የወባ በሽታ ስርጭትን በዘላቂነት መቀነስ እንዲቻል በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የከምባታ ዞን ጤና መምሪያ አስታወቀ።

በዞኑ ዱራሜ ከተማ አስተዳደር 27 ሺህ አጎበር ለህብረተሰቡ መሰራጨቱ ተመላክቷል።

የክረምት ወራት መጠናቀቅ ፈሳሽን ጠርጎ የሚወስድ ዝናብ ባለመኖሩ የወባ ትንኝ እንድትራባ ምቹ ሁኔታን የሚፈጥርና የበሽታውን ስርጭት የሚያባብስ በመሆኑን ከዘርፉ ባለድርሻ አካላት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

በወባ ትንኝ ንክሻ ምክንያት ከህመምተኛው ሰው ወደ ጤነኛው የሚተላለፈው የወባ በሽታ በጊዜ ህክምና ካልተደረገለት ገዳይ እንደሆነም መረጃዎቹ ያመላክታሉ።

በከምባታ ዞን በዱራሜ ከተማ አጎበር ሲቀበሉ አግኝተን ያነጋገር ናቸው ወ/ሮ አምሳለ ሄራሞና አቶ ተስፋዬ ዋንጎሬ በጤና ኤክስቴንሽኖች በተፈጠረላቸው ግንዛቤ መሰረት የበሽታውን ስርጭት ለመቀነስ አጎበሩን በአግባቡ እንደሚጠቀሙ ገልጸዋል።

የታቆሩ ውሃዎችን በማፋሰስ የግልና የአካባቢያቸውን ንጽህና እንደሚጠብቁ ገልጸው፥ አጎበር ማግኘታቸው እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል።

ሲስተር ታገሰች ተስፋዬ እና ወይዘሮ ወርቄ አንበሴ በዱራሜ ከተማ አስተዳደር በተለያዩ ቀበሌያት የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች ሲሆኑ የወባ በሽታ ስርጭት መጨመሩን አስመልክቶ ህብረተሰቡ በተቀናጀ መልኩ የመከላከል ስራ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ህብረተሰቡ ከእንሰት ተክል አንስቶ ውሃ ሊያቁሩ የሚችሉ ገሎችን ከአከባቢ በማራቅ፣ የታቆሩ ውሃዎችን በማፍሰስ እና በማዳፈን፥ የሚሰጡ አጎበሮችን በአግባቡ እንዲጠቀሙ በርካታ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች እንደተሰሩ ተናግረዋል።

ከ 2017 ዓ.ም ጀምሮ የወባ በሽታ ስርጭት ወደ ወረርሽኝ ደረጃ ማደጉን የገለጹት የከምባታ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ ዶክተር ራመቶ አቦ እንደ ዞን በሽታውን ለመከላከል ዘርፈ ብዙ ስራዎች እንደተከናወኑ ተናግረዋል።

በዞኑ ካሉ ከ13ቱ መዋቅሮች በሰባቱ ወረዳዎች የወባ በሽታ በወረርሽኝ መልክ መከሰቱን ተናግረው በክረምቱ መባቻ የታቆሩ ውሃዎችን ከማፋሰስ በተጨማሪ ያሉ አጎበሮችን ለህብረተሰቡ የማዳረስና የኬሚካል ርጭት ስራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል።

በዘንድሮ አመት እንደዞን ለዱራሜ ከተማ አስተዳደር ብቻ 27 ሺህ አጎበር መሰራጨቱን በመግለጽ በቀጣይም ለሌሎች የዞኑ ከተሞች እና ወረዳዎች ለማዳረስ ከክልል እና ከፌደራል ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ በመሆን እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

እንደ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በከምባታ ዞን የቃጫ ቢራ ወረዳ ለወባ በሽታ በከፍተኛ ደረጃ ከተጋለጡ ወረዳዎች የመጀመሪያው መሆኑን የገለጹት ዶክተር ራመቶ የኬሚካል እና የአልጋ አጎበር አቅርቦት በዞን አቅም ማዳረስ ያለመቻል ለበሽታው መስፋፋት ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል።

ክልላዊ የአጎበር ስርጭቱ ከዚህ ቀደም በነበረው የበሽታው ስርጭት ሪፖርት መሰረት የተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል።

የአልጋ አጎበር ለነፍስ ጡር እናቶችና እድሜያቸው ከ 5 አመት በታች ለሆኑ ህፃናት በቅድሚያ እንደሚሰጥ ገልጸው አጎበርን ከታለመለት ዓላማ ውጭ የሚጠቀሙ አካላት በእድር፣በእምነት ተቋማትና በሌሎችም የጋራ የህዝብ ክምችት አጋጣሚዎች በተፈጠረ ግንዛቤ መሠረት በህግ አግባብ እንደሚቀጡም አስገንዝበዋል ።

አንድ አጎበር ከ3-5 ዓመት ድረስ ያገለግላል ያሉት ኃላፊው ህብረተሰቡ ሲቀደድ ሰፍቶና ሲቆሽሽም አጥቦ በጥላ በማስጣት እንዲጠቀምና በዚህም የወባ በሽታን ስርጭት ለመቀነስ በሚደረጉ ጥረቶች የድርሻውን እንዲወጣ መልክት አስተላልፈዋል።

ዘጋቢ: ኤደን ተረፈ – ከሆሳዕና ጣቢያችን