የክረምት በጎ ፈቃድ አንድ አካል የሆነው የቡርጂ ዞን ሶያማ ከተማ አስተዳደር ሲካሄድ የሰነበተው የእግር ኳስ ሻምፒዮና የማጠቃለያ መርሃ-ግብር ተካሂዷል

የክረምት በጎ ፈቃድ አንድ አካል የሆነው የቡርጂ ዞን ሶያማ ከተማ አስተዳደር ሲካሄድ የሰነበተው የእግር ኳስ ሻምፒዮና የማጠቃለያ መርሃ-ግብር ተካሂዷል

‎ማጠቃለያ ጨዋታውን በንግግር ያስጀመሩት የሶያማ ከተማ አስተዳደር ማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ አቶ መሀመድ ህርቦ እንደተናገሩት፤ ውድድሮቹ ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት የሚያስችሉ እንደሆነ በመጥቀስ ተጫዋቾች አቅማቸውንና ችሎታቸውን በአግባቡ ማሳየት ይገባቸዋል።

‎ስፖርት ለወዳጅነት፣ ለጤንነት እና ለሰላም ያለው ጠቀሜታ ከፍተኛ እንደሆነ የገለፁት አቶ መሐመድ፤ ተጫዋቾች ለበጋው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት አካል ለሆነው ውድድር ሊዘጋጁ ይገባል ብለዋል።

‎በቡርጂ ዞን ሶያማ ከተማ በእግር ኳስ ስፖርት እምቅ አቅም ያላቸው በርካታ ስፖርተኞች ያሉ እና በትኩረት ከተሠራ ከአካባቢያቸው አልፈው ከፍተኛ ቦታ ሊደርሱ የሚችሉ ወጣቶች የታዩበት ውድድር ነበር ያሉን ደግሞ የሶያማ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ፍስሃ አድማሱ ናቸው።

‎ከክረምትም በበጋም የስፖርት ውድድር ሲካሄድ ወጣቶች አልባሌ ቦታ እንዳይውሉ እና በጥሩ ስነ-ምግባር እንዲታነፁ ዓላማ ያደረገ መሆኑን ከንቲባው አቶ ፍስሃ አድማሱ አክለው ተናግረዋል።

‎ከተጫዋቾች መካከል ወርቃገኘሁ ወየሳ እና አላሰየም ኡመር ፤ ጨዋታው በጣም አዝናኝ እንደነበር እና ለቀጣይ የበጋው ውድድርም ጠንክረው እንዲሠሩ ያነሳሳቸው እንደሆነ ተናግረው የከተማ አስተዳደሩ ውድድሮችን ከማዘጋጀት ጎን ለጎን የማዘውተሪያ ቦታዎችን እንዲያዘጋጅላቸው ጠይቀዋል።

‎የክረምት ወራት በጎ ፈቃድ ማጠቃለያ አካል የሆነው የእግር ኳስ ጨዋታው በከተማው በሚገኙ በ7 ቡድኖች መካከል ለአንድ ወር ሲካሄድ የቆየው መርሐግብር “ጋሻራ ሲቲ እግር ኳስ ቡድንን ከሻኬ ሲቲ እግር ኳስ ቡድን ጋር ያገናኘ ሲሆን ጋሻራ ሲቲ” የእግር ኳስ ቡድን 2 ለ 1 በማሸነፍ የዋንጫ ተሸላሚ ሆኗል።

‎የውድድሩ ምስጉን ቡድን በመሆን “አየለ ገልዶፍ መታሰብያ” የእግር ኳስ ቡድን ተሸላሚ ሲሆን በውድድሩ የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት የእውቅና እና የምስክር ወረቀት ተሰጥቶ የጨዋታው ማጠቃለያ ሆኗል።

‎ዘጋቢ: ወርቅአገኘሁ ወልደየስ – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን