የችሎት መዝገብ ስራ በቴክኖሎጂ የታገዘ በማድረግ የደንበኞቹን እርካታ ለማሳደግ እየሰራ መሆኑን የጋሞ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ገለፀ

የችሎት መዝገብ ስራ በቴክኖሎጂ የታገዘ በማድረግ የደንበኞቹን እርካታ ለማሳደግ እየሰራ መሆኑን የጋሞ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ገለፀ

ሀዋሳ፡ ጥቅምት 05/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) የችሎት መዝገብ ስራ በቴክኖሎጂ የታገዘ በማድረግ የደንበኞቹን እርካታ ለማሳደግ እየሰራ መሆኑን በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የጋሞ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት አስታወቀ፡፡
‎ፍርድ ቤቱ ከ2 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የገዛውን ዲጂታል መቅረጸ ድምጽ፣ የአገልግሎት ተአማኒነትን እንደሚያረጋግጥ ታውቋል።

‎በጋሞ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ትራንስክራይቨር ባለሞያ ወ/ሮ ሙሉወርቅ ኢሳያስ፥ የተቋሙ ደንበኞችን ድምጽ ቀርጾ ወደ ጽሁፍ የመለወጡ ሂደት አድካሚ እንደነበር ገልፀው አሁን ፍርድቤቱ የሚጠቀምበት ዲጂታል መቅረጸ ድምጽ ቀናትን ይፈጅ የነበረውን አገልግሎት በደቂቃዎች እንዲያልቅ አስችሏል።

‎በጋሞ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሚዲያ ቴክኖሎጂ ባለሞያ አቶ ሰላምይሁን አሊ፥ የፍትህ አገልግሎት አሰጣጥ አስተማማኝነትን እና ቅልጥፍናን ለማሳለጥ የተገዛው ዲጅታል መቅረጸ ድምጽ ዓለም አሁን የደረሰበት ቴክኖሎጂ መሆኑን ጠቁመዋል።

‎የጋሞ ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት የመስማትና መወሰን ዋና ስራ ሂደት አስተባባሪ ወ/ሮ መሃሪነሽ አየለ፥ ከፍርድ ቤቱ ደንበኞች ብዛት፣ የሰው ሃይል ማነስ እና ድምጽን ወደ ጽሁፍ የመቀየሩ ሂደት ዘመናዊ ባለመሆኑ አንድ መዝገብ ለተደጋጋሚ የጊዜ ስለሚቀጠር ደንበኞች ለእንግልት ሲዳረጉ እንደነበር ገልጸዋል።

‎የጋሞ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዘዳንት አቶ የሽመልስ ጮራ፥ የፍትህ አገልግሎት አሰጣጡ ተገልጋዮች ላይ የሚደርሰውን አላስፈላጊ ወጪ እና እንግልት ለማስቀረት የችሎት መዝገብ ስራን በቴክኖሎጂ የታገዘ ለማድረግ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶታል።

‎እንደ አቶ ሽመልስ ገለጻ ፍርድ ቤቱ አሁን ወደስራ ያስገባው የመቅረጸ ድምጽ ቴክኖሎጂ በሃገር ደረጃ አዲስ መሆኑን አስታውሰው፥ የአገልግሎት አሰጣጡን ተአማኒ፣ ተገማች እና ቀልጣፋ ለማድረግ ያለው አበርክቶ ከፍተኛ ነው ብለዋል።

‎ፍርድ ቤቱ የዲጂታል መቅረጸ ድምጽ ባለቤት እንዲሆን የጋሞ ዞን አስተዳደር 2 ሚሊየን 330 ሺ ብር በጀት በመፍቀድ ስላበረከተው አስተዋጾ አመስግነው፥ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፈጣን ግዢ እንዲፈፀም አስተዋጽኦ ማበርከቱን አብራርተዋል።

‎ዘጋቢ፡ አሰግድ ተረፈ – ከአርባምንጭ ጣቢያችን