ትምህርት ቁልፍ የእድገት መሳሪያ ነው የሚለው ተደጋግሞ የተነሳና አሰልቺ የሚመሰል ጉዳይ ነው፡፡ አሰልቺም ቢሆን ተደጋግሞ መነሳቱ ግን አይቀርም፡፡
ለትምህርት ዘርፍ የሚሰጠው ትኩረት የትምህርት ፖሊሲ ከመቅረፅ ይጀምራል። የስርዓተ ትምህርት ዝግጀት ይቀጥላል። ከስርዓተ ትምሀርት ዝግጅት በኋላም መረዳትና መግባባት ለመፍጠር ውይይቶች፣ ስልጠናዎች ሊከናወኑ ይችላሉ፡፡ መቀጠል እንችላለን፡፡ የተግባር ዝርዝሮቹን ለማንሳት ግን ስፍራም ጊዜም ይገድበናል፡፡
ትልቁ ቁም ነገር ግን ብዙ ባለድርሻዎች ያሉት የዓይምሮ ልማት ዘርፍ መሆኑን አለመዘንጋት ነው፡፡ በዚህ ግዙፍ የሰው ሀይል ልማት ኢንዱስትሪ ውስጥ ተገቢነት ያላቸው ነገሮች እንደሚፈፀሙ ሁሉ ተገቢነት የሌላቸውም ተግባራትም ይፈፀማሉ፡፡ ተገቢነት ያለው ስንል ለምሳሌ ያህል በራስ አቅም ብቻ ፈተናን ለመወጣት የሚደረግ ጥረት፡፡ ተገቢነት የጎደለው ኩረጃ፡፡ ተገቢ ትምህርትን ማቅረብ ብቻ ሳይሆን ፈተናንም በተገቢው መንገድ ማስተዳደር አስፈላጊ ነው።
ፈተናን የማስተዳዳር የቀደመ ልምዳችን ሲፈተሸ ኪሳራዎች የበዙበት ስለመሆኑ ተመራማሪና አጥኚ መሆን አለመጠየቁን ከደረሰብን የቅርብ ጊዜያት የዘርፍ ውድቀት አይነተኛ ማሳያ ነው፡፡ በህብረተሰባችን ውስጥ የሚስተዋሉትን ተገቢነት የሌለው ሰርተፍኬት ተሸክሞ ተግባሩን መወጣት ያቃተውን በየአካባቢው በሚገኝ የመንግስት መዋቅር ውስጥ የተሰገሰገውን የሰው ሀይል ማየቱም ሌላኛው አብነት ይሆናል፡፡
የችግሩ ጭንቅላት ደግሞ ፈተናን ከማስተዳደር ጋር የተየያያዘ ነው፡፡ በተለይም ችግሩ ጥርስ አውጥቶ አግጦ የታየው ፈተናን የማስተዳዳር ስርዓቱ እየጠነከረ ሲሄድ ነው። እዚህም እዚያም ጫጫታዎች በረከቱ። አንፈተንም የሚል እንቢተኝነትን ጨምሮ የፈተና አስተዳደር ስርዓቱ ጠበቅ ማለት ፖለቲካዊ ቅርፅ ለማስያዝ ሙከራዎች ተደርገው ነበር፡፡ ሙከራዎቹ ግን ከሽፈዋል፡፡
አሁንም ፈተናዎች የሚሰጡበት የዓመቱ ትምህርት ማጠናቀቂያ ጊዜ እየቀረበ ነው። ፈተና የማስተዳደሩ ጅምር ስራ ተጠናክሮ መቀጠል ነው አለበት፡፡ የመንግስት አካላት፣ የፀጥታ መዋቅሮች መምህራን ወላጆች ሀላፊነት አለባቸው – በዋነኛነት፡፡ መምህራን ተማሪዎቻቸውን የማብቃት እንጂ በሚያልፈው ተማሪዎች ቁጥር ለመቀየር ማሰብም መነሳትም የለባቸውም፡፡ ወላጆች የልጆቻቸውን ዝግጅትና ውሎ ማጥናት አለባቸው፡፡ ለልጃቸው ማለፍ ከማሰብ በፊት በውጤት ማለፍ ነው መጨነቅ ያለባቸው፡፡
በዚህም ከዝግጅት ጀምሮ ፈተና ለማስተዳደሩ ተግባር ተባባሪዎች መሆን አለባቸው፡፡ የተገቢነትን ነገር ካነሳን አይቀር በቅርቡ መነጋገሪያ እየሆነ ያለው የግል ትምህርት ቤት ክፍያ ጉዳይ ነው፡፡ እርግጥ ነው የገንዘብ የመግዛት አቅም እየተዳከመ መጥቷል፡፡ ትምህርት ቤቶቹ በስራቸው የሚያስተዳድሯቸው በርካታ ሰራተኞች አሏቸው፡፡ ሰራተኞቹ የኑሮ ውድነት ማካካሻ ጥያቄዎች ሊኖሯቸው ይችላል፡፡ በዚህ ምክንያት ብቻ የትምህርት ቤት ክፍያን ማሻሻል አስፈላጊነት ማንሳት ይቻላል፡፡
ይህንን ምክንያት በማድረግ ግን አንዳንድ ትምህርት ቤቶች ተገቢ ያልሆነ ክፍያ ለማስከፈል የሚራኮቱ ፣ መቶ ፐርሰንት ጭማሪ የክፍያ ገንዘብ እናስከፍላለን እያሉ ከወዲሁ ወስነው የተነሱ ትምህርት ቤቶች መኖራቸው እየተሰማ ነው፡፡
እነዚህ ትምህርት ቤቶች የሚሰጡት ትምህርት ከሀገሪቱ ካሪኩለም የተለየና ተዓምራቶች የተጨመሩበት ለማስመሰልም ይሞክራሉ፡፡ ይህ ፍላጎት አግባብም ተገቢም አይደለም፡፡ ይህን አግባብነት የሌለው እንቅስቃሴ መንግስት ወላጆችና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት መከላከል መቻል አለባቸው፡፡ ትምህርትን በሁሉም መንገዶች የተገቢነት መሰረት እንዲኖረው ማድረግ የጊዜው ጥያቄ ነውና ሁላችንም ሃላፊነታችንን እንወጣ!
More Stories
በከተሞች የሚስተዋሉትን የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለመፍታት ለሚደረገው ጥረት ህብረተሰቡ ሰፊ ድርሻ እንዳለው ተገለጸ
ማህበራዊ ሚዲያን በአግባቡ በመምራት እና በመጠቀም የአካባቢን ገጽታ መገንባት እንደሚገባ ተጠቆመ
የአዳሪ ትምህርት ቤቶች መስፋፋት ጥራት ያለው ተወዳዳሪ ዜጋ ለማፍራት እንደሚያስችል ተገለጸ