በቤንች ሸኮ ዞን የወባ በሽታ ስርጭት እየተባባሰ መቀጠሉን የዞኑ ጤና መምርያ አስታወቀ

ሀዋሳ፡ ሰኔ 16/2015 ዓ.ም (ደሬቴድ) በቤንች ሸኮ ዞን የወባ በሽታ ስርጭት እየተባባሰ መቀጠሉን የዞኑ ጤና መምርያ አስታወቀ፡፡

መምርያው በዞኑ በ4 ወረዳዎች በወረርሽኙ ዙርያ ያካሄደውን የዳሳሳ ጥናት ውጤት ከባለድርሻ አካላት ጋር ገምግሟል፡፡

በደቡብ ምዕራብ አትዮጵያ ህዝቦች ክልል በቤንች ሸኮ ዞን የወባ በሽታ ስርጭት እየተባባሰ መቀጠሉን የዞኑ ጤና መምርያ አስታውቀዋል፡፡

በዞኑ የበሽታ መከላከል እና መቆጣጠር ዋና ዳይሬክተርና የዳሳሳ ጥናቱ አቅራቢ አቶ ነጋሪ ኮስቲያብ እንደተናገሩት በዞኑ ሚዛን አማን ከተማ አስተዳደር፣ ደቡብ ቤንች፣ ጉራፈረዳ እና ጊዲ ቤንች ወረዳዎች ጥናቱ ተካሂዷል፡፡

በተለይ አጎበርን  በአግባቡ  አለመጠቀም፣ ለወባ ትንኝ መራቢያ ምቹ የሆኑ አካባቢዎችን በተገቢው ያለመድፈንና ያለማጽዳት እንዲሁም የማህበረሰቡ ግንዛቤ አንስተኛ መሆን ለወባ ወረርሽኙ መስፋፋት ምክንያት መሆኑን በጥናቱ እንደተረጋገጠም ገልጸዋል፡፡

በዞኑ የግልን ሳያካትት በመንግስት ጤና ተቋሟት ብቻ ከተመረመሩት 198ሺህ 117 ሰዎች ውስጥ ከ50 በመቶ በላይ ሰዎች የወባ በሽታው ተጠቂ መሆናቸውንም አመልክተዋል፡፡ 

በየደረጃው የሚገኙ ባለድርሻ አካላት ወረርሽኙን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ያሳዩት ቁርጠኝነት አንሰተኛ መሆን፣ ተቀናጅቶ እስከ ቀበሌ ድረስ በመውረድ ተግባሩን በሚገባ ባለመደገፉ እንዲሁም የጤና ኤክስቴንሽን ትግባራ በመቀዛቀዙ ምክንያት ችግሩ ሊስፋፋ እንደቻለም የዞኑ ጤና መምርያ ኃላፊ ተወካይ አቶ ብሩክ ሻዋታጠቅ ገልጸዋል፡፡

ጥናቱ በተደረገባቸው ወረዳዎች ብቻም ሳይሆን አሆን ላይ በዞኑ  ሁሉም ወረዳዎች የወባ ወረርሽኝ በስፋት ተከስቶ ለጤና ስጋት ወደ ሚሆንበት ደረጃ መደረሱንም አስታውቀዋል።

አሁን ካለበት የበሽታው ስርጭት ተባብሶ እንዳይቀጥል ህብርተሰብን ያሳተፈ የአካባቢ ፅዳትና የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ቀጣይ በትኩረት እንደሚሰሩም አቶ ብሩክ ጠቁመዋል።

የመደረኩ ተሳታፊዎችም በሰጡት አስተያየት  በሽታው በተለይ እንደየአካባቢያቸው የተለያዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደረ መሆኑን ገልጸው ወረርሽኙን ለመገታት ትኩረት ሰጥተው እንደሚሰሩም አመልክተዋል፡፡

የዞኑ ብልጽግና ፓርት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ዮናስ ኬና በበኩላቸው የወባ በሽታን የመከላከልና የመቆጣጠር ሥራው ለጤና ሴክተር ብቻ የሚተው ጉዳይ አይደለም ብለዋል፡፡

በዞኑ ያሉ ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች ለወረረሽኙ በጀት በመመደብ ለወባ ትንኝ መራቢያ ምቹ የሆኑ አካባቢዎችን በዘመቻ የማጽዳት ተግባርን ጨምሮ በአንዳንድ የግል ጤና ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮች ፈጥኖ መታረም እንደሚገባ አቶ ዮናስ አሳስበዋል፡፡

ዘጋቢ፡ በየነ ወርቁ – ከሚዛን ጣቢያችን