በወላይታ ዞን በካዎ ኮይሻ ወረዳ ላሾ ጤና ጣቢያ በሚደረግላቸው የወሊድ ክትትልና ድጋፍ ሥራ መደሰታቸውን የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እናቶች ተናገሩ

በወላይታ ዞን በካዎ ኮይሻ ወረዳ ላሾ ጤና ጣቢያ በሚደረግላቸው የወሊድ ክትትልና ድጋፍ ሥራ መደሰታቸውን የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እናቶች ተናገሩ

በየጤና ተቋማቱ ከምንጊዜውም በላይ የወሊድ ክትትልና ድጋፍ ሥራ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መሆኑን በወላይታ ዞን ካዎ ኮይሻ ወረዳ ጤና ጥበቃ ጽህፈት ቤት አስታውቋል።

በጤና ጣቢያው አግንተን ካነጋገርቸው እናቶች መካካል ወ/ሮ ፍቅርተ ኤርምያስ እንደሚሉት ከላሾ 01 ቀበሌ ለወሊድ ክትትል ወደ ጤና ጣቢያ ለ3ኛ ጊዜ የመጡ ሲሆን፤ በጤና ጣቢያው በወሊድ ዙሪያ የሚደረግላቸው እንክብካቤ አሁን ላይ እጅግ የተሻለ ነው።

ከባለሙያዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት በሰፊው እየተሰጠ መቆየቱን የተናገሩ ሲሆን ይህ ክትትል ለእናት ደህንነትና ለልጁም ጤንነት ጥቅሙ የጎላ መሆኑን ነው ያስረዱት።

በከተማው የላሾ ቀራ አካባቢ ነዋሪ ወ/ሮ ኤልሳቤጥ ፋላሃ በበኩላቸው፤ ከዚህ በፊት የወሊድ ክትትልና ድጋፍ አገልግሎት ማግኘታቸውን ገልፀው፤ በተቋሙ በተደረገው ክትትል ለሁለት ዙር በተገቢው እንክብካቤ የወለዱ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በጤና ጣቢያው አዋላጅ ባለሙያ የሆኑት ሲሰተር ቤተልሔም ደበበ እንደሚሉት ለነፍስ-ጡር እናቶች ከቅድመ-ወሊድ እስከ ድህረ-ወሊድ በቂ ክትትል ይደረግላቸዋል።

ከሶስት ወር ጀምሮ በሰላም ተገላግለው ወደ ቤታቸው እስኪመለሱ ድረስ ለእናት ደህንነትና ለልጅ ጤንነት ምቹ ሁኔታ የመፍጠር ሥራዎች በትኩረት ይሠራሉም ብለዋል።

በዕቅድ ደረጃ በ2017 ዓ.ም በጀት ዓመት 2 ሺህ 3 መቶ ለሚሆኑት እናቶች ክትትል በማድረግ ለማዋለድ የታቀደ ሲሆን ከ1 ሺህ 9 መቶ በላይ ለሚሆኑ እናቶች አገልግሎት መስጠት መቻሉን የገለጹት ደግሞ የጤና ጣቢያው የእናቶችና ህፃናት ክፍል አስተባባሪ ሲሰተር ፍሬ ሕይወት ገበየሁ ናቸው።

የላሾ ጤና ጣቢያ ዋና ሥራ አስከያጅ አቶ አቤኒዜር ሴታ በበኩላቸው፤ ከዚህ በፊት በርካታ እናቶች እቤት በመውለድ ለሞትና ከወሊድ ጋር ተያይዞ ለሚመጡ ችግሮች የሚጋለጡ እንደነበሩ ተናግረዋል።

በአሁን ወቅት ግን መንግስት ባመቻቸው መልካም ዕድል በመጠቀም ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መሆኑን አስረድተዋል።

በወላይታ ዞን ካዎ ኮይሻ ወረዳ ጤና ጥበቃ ጽ/ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ዳዊት ዳልከ፤ በወረዳ ደረጃ ሁለት ጤና ጣቢያ ሲኖሩ፤ የአንዳንድ አካባቢዎች የመሬት አቀማመጥ ለአምቡላስ አገልግሎት ምቹ ባለመሆኑ ምክንያት ከስምንት ወር ጀምረው በተዘጋጀው ማቆያ እንዲቆዩ በማድረግ የማዋለድ ሥራ እንደሚደረግ ገልጸዋል።

በወረዳ ደረጃ የ1ኛ ደረጃ ሆስፒታል ባለመኖሩ ምክንያት ከጤና ጣቢያ አገልግሎት በተሻለ የሕክምና አገልግሎት ለሚፈልጉ ታካሚዎች ከአጎራባች ወረዳዎች ጋር ውል ተፈራርመዋል እየሠሩ እንዳለም ጠቁመዋል።

ዘጋቢ፡ ያስን ጫታላ – ከዋካ ጣቢያችን