የተሻለ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተደራሽ በማድረግ ህብረተሰቡ በበዓል ወቅት ያልተቆራረጠና ደህንነቱ የተጠበቀ አገልግሎት እንዲያገኝ በትኩረት እየሠራ መሆኑ ተገለጸ
ሀዋሳ፡ መስከረም 15/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) የተሻለ የኤሌክትሪክ አገልግሎትን ተደራሽ በማድረግ ህብረተሰቡ በበዓል ወቅት ያልተቆራረጠና ደህንነቱ የተጠበቀ አገልግሎት እንዲያገኝ በትኩረት እየሠራ መሆኑን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ሪጅን ኤሌክትሪክ አገልግሎት ጽ/ቤት አስታወቀ ።
በበዓላት ወቅት ከተለመደው ጊዜ ለየት ባለ ሁኔታ ከፍተኛ የሆነ የኤሌክትሪክ አጠቃቀምና የኃይል ፍጆታ ስለሚኖር ህብረተሰቡ ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባም ጽ/ቤቱ አሳስቧል ።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ሪጅን ኤሌክትሪክ አገልግሎት ጽ/ቤት የኔትወርክ ኢንፍራስትራክቸር ኃላፊና የዳይሬክተሩ ተወካይ አቶ ፍሬው ገዛኸኝ እንደገለፁት እንደተቋም ህብረተሰቡ በበዓላት ወቅትም ይሁን በሌሎች ጊዜያት ደህንነቱን የተጠበቀ የኤሌክትሪክ አገልግሎት እንዲያገኝ ዘርፈ ብዙ ሥራዎች እየተሠሩ ነው ።
በበዓላት ወቅት ከተለመደው ጊዜ ላቅ ያለ የኤሌክትሪክ ፉጆታ እንደሚኖር የጠቆሙት ኃላፊው፥ ለዚህም ያልተቆራረጠና ደህንነቱ የተጠበቀ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ለመስጠት በክልሉ በሆሳዕና ፤ በወልቂጤ፣ በቡታጅራና በሌሎች አከባቢዎች የጥገና ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸውን አብራርተዋል ።
ከኃይል ጋር ተያይዞ የሚስተዋለውን ችግር ለመፍታትና ለማመጣጠን ሰፊ ርብርብ እየተደረገ መሆኑንም አቶ ፍሬው አሳውቀዋል ።
አቶ ፍሬው አክለውም የመስቀል በዓልን ተከትሎ በዘርፉ ሊከሰቱ የሚችሉ ችግሮችን ለመፍታትና የደምበኞችን ጥሪ ለማስተናገድ የሚያስችል የባለሙያ ቡድን ኮማንድፖስት በክልሉ በ28 ማዕከላት ተመድበው እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን አስረድተዋል ።
በበዓላት ወቅት ከተለመደው ጊዜ ለየት ባለ ሁኔታ ከፍተኛ የሆነ የኤሌክትሪክ አጠቃቀምና የኃይል ፍጆታ ስለሚኖር ህብረተሰቡ የራሱን የቤተሰቡንና የንብረቱን ደህንነት ለመጠበቅ አጠቃቀሙን ጥንቃቄ በተሞላ መልኩ ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በተለይ የቤት ውስጥ የኤሌክትሪክ ኃይል መገልገያ ዕቃዎችን ሁሉን በአንድ ጊዜ አለመጠቀምና ለኃይል ቁጠባ አማራጭ ሰዓቶችን በመጠቀም ለአገልግሎቱ መሳለጥ ህበረተሰቡ የበኩሉን እንዲወጣም አቶ ፍሬው ጠይቀዋል።
ችግሮች ከተፈጠሩ ወዲያው ለተቋሙ በማሳወቅ በተቋሙ በለሙያዎች ብቻ እንዲፈታ ማድረግ እንደሚገባ አስታውቀዋል ።
ከተቋሙ ባለሙያዎች እና ከተፈቀደለት አካል ውጪ ኤሌክትሪክ መነካካት በሰው ህይወትና በተቋሙ መሠረተ ልማቶች ላይ ጉዳት ከማድረሱም ባለፈ በወንጀልም ስለሚያስጠይቅ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አቶ ፍሬው አሳስበዋል ።
በመጨረሻም ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች ለመስቀል በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ዘጋቢ: መልካሙ ታፈሰ – ከሆሳዕና ጣቢያችን
More Stories
የማታ 1፡00 ዜና 24፤ ሀዋሳ፡ ጥቅምት 04/2018 ዓ.ም
ጃፓን በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ብራዚልን አሸነፈች
ከተሞች በዲጂታል ቴክኖሎጂ ታግዘው አገልግሎት መሥጠታቸው የተገልጋይና የአገልጋይ ግንኙነት ጤናማና እርካታ የተሞላበት እንዲሆን የሚያስችል መሆኑ ተገለጸ