የቦንጋ ኤፍ ኤም 97.4 ቅርንጫፍ በጣቢያው የልጆች ፕሮግራም ለሚያዘጋጁ ህጻናት የመማሪያ ቁሳቁስ አበረከተ

የቦንጋ ኤፍ ኤም 97.4 ቅርንጫፍ በጣቢያው የልጆች ፕሮግራም ለሚያዘጋጁ ህጻናት የመማሪያ ቁሳቁስ አበረከተ

ሀዋሳ፡ መስከረም 15/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) በደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት የቦንጋ ኤፍ ኤም 97.4 ቅርንጫፍ በጣቢያው የልጆች ፕሮግራም ለሚያዘጋጁ ህጻናት የመማሪያ ቁሳቁስ አበረከተ፡፡

የመማሪያ ቁሳቁስ የተበረከተላቸዉ ህጻናት ድጋፉ በቀጣይ የተሻለ እንድንሰራ የሚያበረታታን ነዉ ብለዋል።

ጣቢያው ለአድማጮቹ ከሚያደርሳቸዉ ተወዳጅ ፕሮግራሞች መካከል ዘወትር ቅዳሜና እሁድ ጠዋት የሚተላለፈዉ የህጻናት ፕሮግራም አንዱ ነዉ።

ስጦታዉን ያበረከቱት የተቋሙ ምክትል ስራ አስኪያጅ እና የይዘት ዘርፍ አስተባባሪና አቶ አሸናፊ ዓለሙ ፤ የቦንጋ ኤፍ ኤም 97.4 ከተሰጠዉ የማስተማር፣ የማሳወቅና ማዝናናት ተልዕኮ በተጨማሪ ማህበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል ብለዋል።

በተለይም በይዘት ደረጃ ወደ አድማጮቹ እየደረሰ በሚገኘዉ የህጻናት ፕሮግራም ልጆች ስለ አካባቢያቸዉ በቂ እዉቀት እንዲኖራቸዉና የአፍ መፍቻ ቋንቋቸውን በቀላሉ እንዲረዱ ያስቻለ መሆኑንም ተናግረዋል።

መሰል ዕድሎች ህጻናት ከአልባሌ ቦታ ተጠብቀው ስራን እየተለማመዱ እንዲያድጉ ይረዳል ያሉት አስተባባሪዉ ፤ የተሰጣቸዉ የመማሪያ ቁሳቁስ በቀጣይ የተሻለ ተነሳሽነት እንዲኖራቸዉ በማሰብ መሆኑን ገልጸዋል።

በፕሮግራሙ ላለፉት በርካታ ጊዜያት እየተሳተፉ መቆየታቸዉን የተናገሩት ተማሪ ቤዛዊት ታዬ እና ፋሲካ ግርማ በቀጣይ ጋዜጠኛ የመሆን ህልም እንዳላቸዉ ገልጸው ፤ ለዚህም ዕድለኛ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

የተሰጣቸዉ የመማሪያ ቁሳቁስም በስራቸዉ ትጉህ እንዲሆኑ የሚያነሳሳቸዉ እንደሆነም አስተያየታቸዉን ሰጥተዋል።

ዘጋቢ፡ በአሰግድ ሣህሌ – ከቦንጋ ጣቢያችን