የመስቀል ደመራ በዓል ስናከብር በአንድነትና በፍቅር ሊሆን ይገባል – የኮሬ ዞን ቤተክህነት

የመስቀል ደመራ በዓል ስናከብር በአንድነትና በፍቅር ሊሆን ይገባል – የኮሬ ዞን ቤተክህነት

መስቀል ኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅሩን ለእኛ ያሳየበት በመሆኑ በአንድነትና በፍቅር ልናከብር ይገባናል ሲል የኮሬ ዞን ቤተ ክህነት አስታወቀ።

የኮሬ ዞን ቤተ ክህነት ስራ አስኪያጅ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታረቀኝ ሙቃ፥ መስቀል ደመራ በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ትልቅ ቦታ የሚሰጠውና በድምቀት የሚከበር የአደባባይ በዓል መሆኑን ገልጸዋል።

ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ሞቶ ፍቅሩን ለእኛ አሳይቷል ያሉት ቀሲስ ታረቀኝ እኛም በፍቅርና በአንድነት ከሁሉም ጋር እናከብራለን፤ ስናከብርም ቆይተናል ብለዋል።

በዓሉን ከሰንበት ተማሪዎች፣ ከካህናት፣ ከምዕመናንና አጠቃላይ ከማህበረሰቡ ጋር በድምቀት ለማክበር አስፈላጊ የሆኑ ዝግጅቶች መደረጋቸውን ጠቁመዋል።

ይህን በዓል በተለያዩ የባህል አልባሳት ደምቀን፣ ልዩነቶችን በማጥበብና አንድነትን በማጠናከር፣ ፍቅርን ለሌሎች በማካፈል ማክበር አለብን ሲሉ ተናግረዋል።

በመጨረሻም ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች እንኳን ለብርሃነ መስቀሉ በሰላም አደረሳችሁ በማለት መልካም ምኞታቸውን አስተላልፈዋል ።

ዘጋቢ: ለምለም ኦርሳ – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን