የተቋሙን አሰራር በማሻሻል አለም አቀፍ ስታንዳርድ ያሟላ ተወዳዳሪ ተቋም እንዲሆን እየተሰራ መሆኑን የሆሳዕና ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ አስታወቀ

የተቋሙን አሰራር በማሻሻል አለም አቀፍ ስታንዳርድ ያሟላ ተወዳዳሪ ተቋም እንዲሆን እየተሰራ መሆኑን የሆሳዕና ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ አስታወቀ

በኮሌጁ “ISO 21001: 2018” የትምህርት ተቋማት አስተዳዳር ስርዓት “EOMS” የሙከራ ትግበራ ማስጀመሪያ መርሃግብር ተካሂዷል።

የሆሣዕና ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ዲን አቶ አወል ሸንጎ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ በኮሌጁ ISO 21001: 2018 የትምህርት ተቋማት አስተዳዳር ስርዓትን ለመተግበር ከኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት ጋር ውል በመግባት እየተሰራ ይገኛል።

የኮሌጁን አሰራር በማሻሻል ወደ አለማቀፋዊ ስታንዳርድ በመግባት ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ መሆን ያስፈልጋል ያሉት የኮሌጁ ዲን፤ ለዚህም የሙከራ ትግበራ ማስጀመሪያ መርሀ-ግብር መካሄዱን ገልጸዋል።

ኮሌጁም ከሙከራ ትግበራ ወደሙሉ ትግበራ ሲገባ ለተቋሙ ዘርፈ ብዙ አለም አቀፋዊ ጠቀሜታ እንዳለው አስረድተዋል።

ትግበራውን ውጤታማ በማድረግ ተቋሙን፣ የተቋሙን አሰልጣኞች እና ሰልጣኞችን አለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ደረጃ እንዲገቡ በሁሉም የኮሌጁ ማህበረሰብ በኃላፊነት እንዲሰራም አቶ አወል ጥሪ አስተላልፈዋል።

በኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት የስልጠናና ቴክኒክ ድጋፍ ባለሙያ አቶ ዳንኤል ገብረ እግዚአብሔር ስለትግበራው ገለፃ ባደረጉበት ወቅት ISO 21001:2018 የትምህርት ተቋማት አስተዳደር ስርዓቱ ዓለም አቀፍ የአሰራር ስርዓት መሆኑን አስረድተዋል።

የበርካታ ሀገራት ተቋማት ይህን የአሰራር ስርዓት በመተግበራቸው የተገልጋይ እርካታና የምርት ጥራታቸውን በመጨመር በደምበኞቻቸው አመኔታና ተቀባይነት ማግኘታቸውንም ገልጸዋል።

ይህን የአሰራር ስርዓት ተግባራዊ ያደረጉ ቴክኒክና ሙያ ተቋማት የሚገኙ አሰልጣኞች እና ሰልጣኞች በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የመሆን ዕድል እንዳላቸው ገልጸው ኮሌጁም በትኩረት እንዲሰራ አስገንዝበዋል።

በመድረኩ የተገኙት የሀዲያ ዞን ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና መምሪያ ኃላፊ አቶ ተስፋዬ እርስቱ እንደተናገሩት፤ በዞኑ የሚገኙ ሁሉም ቴክኒክና ሙያ ተቋማት ወደ ትግበራው እንዲገቡ እየተሰራ ነው።

ዜጎችን በተለያዩ ሙያዎች በመቅረጽ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለማድረግ ደረጃውን ያሟላ አሰራር ውስጥ መግባት አስፈላጊ በመሆኑ የተጀመረው ስራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ኃላፊው መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

አሰልጣኝ ታሪኩ አዳነ በኮሌጁ የአውቶሞቲቭ ዲፓርትመንት አሠልጣኝና የፈጠራ ስራዎች ባለቤት ሲሆን ተቋሙ ወደትግበራው መግባቱ በዓለም አቀፍ የፈጠራ ስራዎች ውድድር ላይ የመሳተፍ ዕድል እንደፈጠረ ተናግሯል።

በ2017 በቻይና ሀገር በተደረገው የዓለም አቀፍ የፈጠራ ስራዎች ውድድር ላይ ኢትዮጵያን በመወከል ከ1 መቶ 61 ሀገራት ተወዳድሮ 3ኛ ደረጃ መውጣቱን የገለጸው አሰልጣኝ ታሪኩ፤ ኮሌጁ ትግባራውን መጀመሩ ለቀጣይ ስራዎችም አጋዥ መሆኑን አንስቷል።

የተቋሙ ሰራተኞች በበኩላቸው ትግበራው ሙሉ እንዲሆን የሚጠበቅባቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ዘጋቢ፡ ኤርጡሜ ዳንኤል – ከሆሳዕና ጣቢያችን