“ሄቦ” በየም ብሄረሰብ
በደመቀ ጀንበሬ
“ሄቦ” የየም ብሄረሰብ የዘመን መለወጫ ክብረ በዓል (የነጻነት፣ የአንድነትና የዕርቅ በዓል)”
የየም ብሔረሰብ የራሱ ቋንቋ፤ የቀን አቆጣጠር፤ ባህላዊና ታሪካዊ ቅርስ፣ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ብሎም በአፍሪካ ቀደምት የስልጣኔ መነሻ የሆነ ታርክ ያለው ህዝብ እንደሆነ የተሌዩ ዓለም አቀፍ የታሪክ ድርሳናት ያረጋግጣሉ፡፡
‹‹ሄቦ›› ማለት የቃሉ ትርጉም ደስታ፣ብሩ ተስፋ፣ነጻነት፣ ልዩና የዳበረ አዲስ ደስታ ማለት እንደሆነ የጽሁፍ መረጃዎችና የብሄረሰቡ አባቶች ይናገራሉ፡፡
የ‹‹ሄቦ›› በዓል አከባበርን በተመለከተ ታሪካዊ መረጃዎች እንደሚገልጹት ከ3ሺ ዓመት በላይ ታሪክ ያለውና ይኸውም ጥንት የእስራኤላውያን ከግብፅ ባርነት ነፃ መውጣት ጋር ተያይዞ የነፃነት በዓል፤ የምስጋና መታሰቢያ ሆኖ የተጀመረ እና እስከ ዛሬ ድረስ እንደ ዘመን መለወጫነት የሚከበር የብሔሰቡ ክብረ በዓል ነው።
የየም ብሄረሰብ ጥንት የክርስትና እምት ወደ ኢትዮጵያ ከመግባቱ በፊት ጀምሮ ሲያከብረው የነበረውና አሮገውን ዓመት ሸኝቶ አድሱን ዓመት የሚቀበልበት ካለፈው ተምሮ አዲሱን በንፅህና የሚቀበልበት ክብረ በዓል አለው፡፡ ይህ ክብረ በዓል ተደብቆ የነበረውና ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበትን ግማደ መስቀል ንግስት እሌኒ ደመራ አስደምራ ተቆፍሮ የተገኘበት ዝክረ መስቀል በዓል በአጋጣሚ ተገጣጥሞ በየም ብሄረሰብ ዘንድ የሔቦ በዓልና የመስቀል በዓል በአንድ ላይ ይከበራል፡፡
የመስቀል በዓል አብሮ ይከበር እንጂ በብሄረሰቡ ዘንድ በተለያዩ ባህላዊ ሁነቶች ታጅቦ ዘለግ ላሉ ቀናት ጎልቶ የሚከበረው የሄቦ በዓል ነው፡፡
ብሄረሰቡ በዓሉን ለማክበር አስቀድሞ የተለያዩ ዝግጅቶችን ያደርጋል፡፡ የሄቦ ክብረ በዓል መምጣትንም በጉጉት ይጠባበቃል፡፡ መድረሱ አይቀርምና በዓሉ ሊከበር ወራት ሲቀሩት ለክብረ በዓሉ አስፈላጊ የሆኑ ዝግጅቶች በይፋ ይጀመራል፡፡
1. ለሄቦ በኣል የሚደረጉ ቅድመ ዝግጅቶች
1.1.ቁጠባ
በብሔረሰቡ ዘንድ የሄቦ በዓልን ለማክበር የዓመት ዝግጅት ይደረጋል። ለበዓሉ የሚያስፈልግ ምግብ፣ መጠጥና አልባሳት ለመግዛት በዓሉ ሲቃረብ ሊገጥም የሚችለውን መጨናነቅ ለመቅረፍና በበቂ ሁኔታ ዝግጅቱን ለማሳናዳት አባወራዎች፣እማወራዎችና ወጣቶች የገንዘብና እንደ አስፈላጊነቱ የዓይነት ቁጠባ ያደርጋሉ።
የገንዘብ ቁጠባው ለልብስ፣ ለቤት ዕቃ፣ ለቅመማ ቅመምና ለበዓል ምግብ፣ለስጋ በሬ ግዥ የሚውል ነው፡፡
በሄቦ በዓል ወቅት ከብቶችም ጠግበው መክረም ስለሚኖርባባቸው የከብቶች መኖ ሳርም ለረጅም ጊዜ ተከልሎ ማንም ሊያሰማራው የሚይችልበት የእንጨት ምልክት በብሄረሰቡ ቋንቋ (ዛዞ) በሳሩ መሀል ተወግቶ በዓሉ እስኪደርስ ድረስ ሳሩ ይለማል፡፡
ለበዓሉ ማክበሪያ ለመጠጥ የሚሆን ብቅል ማብቄያ እና ለምግብ የሚሆን እህልም በበጋ ወቅት ሰብል ተሰብስቦ በሚወቃበት ወቅት ነው ከአውድማው ለሄቦ በዓል ተብሎ ተለይቶ የሚቀመጠው፡፡ የሄቦ በዓል ለማክበር የይድረስ ይድረስ የሚባል ነገር አይታወቅም፡፡ ለባህላዊ መጠጥ ቦርዴ (የማ ኡሻ) ዝግጅት የሚሆን ብቅል እንኳ የከረመ መሆን አለበት ስለሚባል እናቶች ብቅል ማብቀል የሚጀምሩት በብሄረሰቡ የወራት ስያሜ የብቅል ውር በሚባለው(ቱሉ) ጥር ወር ነው፡፡
ለሄቦ በዓል የሴቶች የስራ ድርሻ
• የኮባና ዝግጅት
ለሄቦ በዓል በዋናነት ከእንስሳት ተዋጽኦ ጋር የሚበላው የቆጮ ድፎ(ኮባና)ነው፡፡በመሆኑም ለሄቦ በዓል የሚሆን ቆጮ ከወትሮው በተለየ መልኩ በልዩ ሁኔታ ሴቶች በደቦ በየተራቸው እንሰት በመፋቅ ጉድጓድ ውስጥ ያከርማሉ፡፡ ታዲ የቆጮ ዝግጅት ስራ በዋናነት የሴቶች ነው፡፡ ቢሆንም ግን በሚፋቅበት ወቅት ወንዶችም የእንሰቱን ቅጠል በመቁረጥ፤አምቾ (የእንሰት ስር)በመንቀል፣በማፅዳትና በመከስከስ እንዲሁም ሌሎች አስፈላጊ ስራዎችን በመርዳት ይተባበራሉ።
በዓሉ ሊከበር ሳምንት ሲቀር ተፍቆ የከረመው ቆጮ ከቆየበት ጉድጓድ ወጥቶ ጥሬ ቆጮ ተቆርጦ ይጠራቀማል፤ከዚያም መስከረም 15 እና 16 ዕለት የቆጮ ድፎ(ኮባና) ይደፋል፡፡ ከመስከረም 17 ዕለት ጀምሮ ተቆርሶ እየተጠበሰ ከእንስሳት ተዋጽኦ ጋር መበላት ይጀምራል፡፡ ይህ ኮባና በዓሉ እስከ ሚያበቃበት ቀን እስከ ወር ድረስ ቆይቶ እየተቆረሰ በስጋ፣ በወተትና በእርጎ እየተበላ በዓሉ ይከበራል።
ለክብረ በዓሉ ከሚዘጋጁ ባህላዊ መጠጦች መካከል ዋነኛው ‹‹ቺፋ›› ወይም የማ ኡሻ(ቦርዴ) ነው። መጠጡ ከገብስና ከቀይ ጤፍ የሚዘጋጅ ሲሆን ሴቶች ቀደም ብለው ከጥር ወር ጀምሮ ለቦርዴው የሚሆን ብቅል አብቅለው ያስቀመጡትን ብቅል በዓሉ ሲቃረብ ከገብስ ወይም ከቀይ ጤፍ ጋር አስፈጭተው ሲያሰናዱ የሚጠጣ ባህላዊ መጠጥ ነው። ይህ ተግባርም ኃላፊነቱ በዋናነት በሴቶች ላይ የተጣለ ነው፡፡
የወጣቶች የስራ ድርሻ
ለሄቦ በዓል በሚደረጉ ዝግጅቶች ሁሉም የቤተሰብ አባል የስራ ድርሻውን ሳይታክትና ሳይሰለች ይወጣል፡፡ የሚታገዝ ካለም በመተጋገዝ መስራት በዓሉ የሚጥለው የውዴታ ግዴታ ነው፡፡
‹‹ዱዋ››(እሳት ማቆ የግንድ ጉማጅ)
ለሄቦ በዓል የሚሆን የማገዶ እንጨት ማዘጋጀት የወጣቶች (የወንዶች) ተግባር ነው፡፡ በሄቦ በዓል ወቅት እሳት ከቤት እንዲጠፋ አይፈቀድም፣ከጎረቤትም አይጫርም፤ ለዚህም እስከ በዓሉ መጠናቀቂያ ድረስ እሳት በቤት ውስጥ ሊያቆይ የሚችል ደርቆ የከረመ የግንድ ጉማጅ ይዘጋጃል፡፡ይህ የግንድ ጉማጅ በየምኛ ‹‹ዱዋ›› ይባላል፡፡ ይህ ‹‹ዱዋ›› ከምሰሶው በላይ በስተጓዳ በኩል ካለው ምድጃ ይቀመጣል። ዱዋ ላይ የተቀጣጠለው እሳት በዓሉ እስኪጠናቀቅ ድረስ ይቆያል። ቢያልቅም በምትኩ እየተተካ ቤቱንም እያሞቀ ይቆያል።
የጎቶ ዝግጅት
ጎቶ፡- በሄቦ በዓል ወቅት የሚውል የማገዶ እንጨት ነው። በበዓሉ ወቅት ልጆች የማገዶ እንጨት ፍለጋ ወደ ጫካ እንዳይሄዱና በዓሉን በነፃነት እንዲያከብሩ ሲባል በዓሉ ሊቃረብ 2 ወር ሲቀረው ዛፍ ተቆርጦ ይጣልና ተፈልጦ ቅርፊቱ ተለይቶ በጎጆ ቅርጽ በተለያየ ቦታ ተከምሮ እየደረቀ ይቆያል። በዓሉ ሲቃረብ ከኮበና ማብሴያ ቀን መስከረም 15 ቀን ጀምሮ ከተከመረበት ወደ ቤት ይጓጓዝና በዓሉ እስኪጠናቀቅ ድረስ ለማገዶነት ይውላል፡፡ በዚህ ወቅት የማገዶ ችግር አይወራም፡፡ይህም ተግባር በዋናነት የወጣቶች ነው፡፡
የቤት እንስሳትም በተለይ መስከረም 16 የሄቦ በዓል ዋዜማ‹‹አሜቱ›› ዕለት ጠግበው ማደር አለባቸው ተብሎ ስለሚታመን የመኖ ሳር አጨዳም የወጣቶች ተግባር ነው፡፡
የሴት ወጣቶችና ልጆች የስራ ድርሻ
በሄቦ በዓል ወቅት የሴት ወጣቶች ዋነኛው የስራ ድርሻ የመኖሪያ ቤትና አካባቢ ማስዋብ፣ አልባሳትና የቤት መገልገያ ዕቃዎችን ማጠብ እንዲሁም በማንኛው የእናቶች ስራ የቻሉትን ያህል ማገዝ ነው፡፡
የአባቶች የስራ ድርሻ
የአባቶች የስራ ድርሻ፡- ለሄቦ በዓል የሚደረጉ ዝግጅቶችን መምራት፣ ለስጋ ተብሎ በእቁብ ተቆጥቦ የተጠራቀመውን ገንዘብ ተከፋፍሎ የስጋ ሰንጋ መግዛትና ለበዓሉ የሚሆን ስጋ ማቅረብ፣ ለልጆች ልብስ መግዛት፣ለእንስሳትም የሚስፈልጋቸው መኖ መዘጋጀቱን መከታተልና እንዲቀርብ ማድረግ ናቸው፡፡
More Stories
የማታ 1፡00 ዜና 24፤ ሀዋሳ፡ ጥቅምት 04/2018 ዓ.ም
ጃፓን በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ብራዚልን አሸነፈች
ከተሞች በዲጂታል ቴክኖሎጂ ታግዘው አገልግሎት መሥጠታቸው የተገልጋይና የአገልጋይ ግንኙነት ጤናማና እርካታ የተሞላበት እንዲሆን የሚያስችል መሆኑ ተገለጸ