በወሊድ ምክንያት በእናቶችና ህጻናት ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ
ሀዋሳ፡ መስከረም 15/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) በወሊድ ምክንያት በእናቶችና ህጻናት ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ እየሰራ መሆኑን የገዋታ ወረዳ ጤና ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
በ2017 በጀት ዓመት ”አንድ ምሳ ለአንድ እናት” በሚል ሀሳብ ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር በላይ በመሰብሰብ በማቆያ ውስጥ ለሚገኙ ነፍሰ ጡር እናቶች የምገባ አገልግሎት መጀመሩንም ገልጿል።
በእናቶች እና ህጻናት ጤና ላይ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ጉዳቶችን ለመቀነስ በቅድመ ወሊድም ሆነ በድህረ ወሊድ ወቅት በጤና ተቋማት አስፈላጊው ምርመራና ህክምና በማድረግ ከፍተኛ ለውጥ መመዝገቡን የዘርፉ ባለሙያዎች ተናግረዋል፡፡
በካፋ ዞን ገዋታ ወረዳ ከሚገኙ ጤና ተቋማት በቆንዳ ጤና ጣቢያ የእናቶች ማቆያ አግኝተን ያነጋገርናቸው ወ/ሮ አበበች አዲሱ እና ገነት ለገሰ ምገባን ጨምሮ ጥሩ አገልግሎት እያገኙ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በጤና ተቋም ሆነው የእርግዝና ጤንነታቸውን በመከታተላቸው ከስጋት ነጻ መሆናቸውን እና ጤናማ ህጻን ታቅፈው እንደሚመለሱ እምነታቸው ጽኑ መሆኑን የተናገሩት እናቶች ይህ አገልግሎት ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት ነዉ ብለዋል።
በጤና ጣቢያዉ ግቢ ዉስጥ በተዘጋጀላቸዉ ማረፍያ ከገቡ ሁለት ሳምንት እንደሆናቸዉ ገልጸዉ፥ በዚህ ቆይታቸዉ የህጻናት ጤና አጠባበቅና አያያዝ የስነ-ምግብና ተዛማጅ ጉዳዮች ላይ ትምህርት እየተሰጣቸዉ መሆኑን ነዉ የተናገሩት።
በቆንዳ ጤና ጣቢያ የእናቶችና ህጻናት ክፍል የጤና ባለሙያ አቶ መሰረት የሺ፥ ነፍሰ ጡር እናቶች ከ36ኛዉ ሳምንት ጀምሮ በጤና ጣቢያዉ የማቆያ ክፍል እንዲሆኑ ተደርጎ ቅርብ ክትትልና የህክምና አገልግሎት እየተሰጠ ነው ብለዋል፡፡
ቀደም ሲል ምግብ በበቂ ሁኔታ ስለማያገኙ በጤና ጣቢያዉ ቆይቶ ለመዉለድ ፍላጎት እንዳልነበራቸዉ የተናገሩት አቶ መሰረት የምገባ ፕሮግራም መጀመሩ ብዙ ለዉጥ እያመጣ በመሆኑ እንዳይቋረጥ ትኩረት ሊደረግ ይገባል ነዉ ያሉት።
የገዋታ ወረዳ ጤና ጥበቃ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አብዱ አባግዲ በበኩላቸዉ፥ በጤና ተቋማት የሚወልዱ እናቶችን ምጣኔ ለማሻሻል እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በ2017 በጀት አመት በወረዳዉ ጤና ተቋማት የወሊድ አገልግሎት ማግኘት ከነበረባቸዉ እናቶች 46 ከመቶ ያህሉ ብቻ መከናወኑን ጠቅሰው፥ ለዚህ መሰረታዊ የሆኑ ችግሮችን በመለየት መፍትሄዎች ላይ እየተሰራ ነዉ ብለዋል ።
በዘርፉ የሚስተዋሉ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን ለመፍታት እና የተለያዩ የህክምና መገልገያ ቁሳቁሶችን ለማሟላት ጥረት እየተደረገ ነዉ ያሉት አቶ አብዱ በቀጣይ የተሻለ ዉጤት ለማስመዝገብ ድጋፍና ክትትሉ ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል ብለዋል።
አዘጋጅ፡ አሳምነው አትርሳው
More Stories
የማታ 1፡00 ዜና 24፤ ሀዋሳ፡ ጥቅምት 04/2018 ዓ.ም
ጃፓን በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ብራዚልን አሸነፈች
ከተሞች በዲጂታል ቴክኖሎጂ ታግዘው አገልግሎት መሥጠታቸው የተገልጋይና የአገልጋይ ግንኙነት ጤናማና እርካታ የተሞላበት እንዲሆን የሚያስችል መሆኑ ተገለጸ