በየትኛውም ዘርፍ ውጤት ለማስመዝገብ የትምህርቱን ዘርፍ በማጠናከር የተሻለ አፈጻጸም ለማስመዝገብ ባለድርሻ አካላት ርብርብ ማድረግ እንደሚገባቸው ተገለፀ
በየትኛውም ዘርፍ ውጤት ለማስመዝገብ የትምህርቱን ዘርፍ በማጠናከር የተሻለ አፈጻጸም ለማስመዝገብ ባለድርሻ አካላት ርብርብ ማድረግ እንደሚገባቸው የጂንካ ከተማ ከንቲባ አቶ ሲሳይ ጋልሺ ገለጹ፡፡
ይህ የተገለጸው በኣሪ ዞን በጂንካ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ጽህፈት ቤት የ2018 በጀት ዓመት 1ኛ ሩብ ዓመት አፈጻጸምና የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር በተደረገው የምክክር መድረክ ላይ ነው፡፡
የጂንካ ከተማ ከንቲባ አቶ ሲሳይ፤ በዘንድሮው አመት በሀገር አቀፍ ደረጃ በተመዘገበው የፈተና ውጤት በክልል ደረጃ ብሎም እንደ ኣሪ ዞን ከፍተኛ ውጤት የተመዘገበው በጂንካ ከተማ አስተዳደር ተማሪዎች በመሆኑ ይህ የትምህርት ባለድርሻ አካላት ጥረት ውጤት መሆኑን አንስተዋል።
በትምህርቱ ስራ መምህራን፣ ርእሳነ መምህራን፣ ሱፐርቫይዘሮች እና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ወሳኝ ሚና የሚጫወቱ በመሆናቸው የተቀናጀና ጠንካራ ስራ ያስፈልጋል ብለዋል።
የጂንካ ከተማ ምክትል ከንቲባና የትምህርት ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ውባለም ገዛኸኝ፤ እንደከተማ አስተዳደር በትምህርቱ ስራ ከግብአት ጀምሮ በርካታ ክፍተት እያለ ከመምህራን ጥረት ጀምሮ በባለድርሻ አካላት ርብርብ እንደዞን ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገባችን ደስታ ተሰምቶናል ብለዋል።
ከሰራን ውጤት እንደምናመጣ አይተናል ያሉት ኃላፊው፤ ለዚህ ውጤት መመዝገብ የተጉ መምህራንና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል።
የኣሪ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ እና የከተማና ቤቶች ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ገረመው ኃይለማርያም በመድረኩ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት፤ ከጊዜ ወደ ጊዜ በትምህርት ስራ ላይ ለውጥ እየተመዘገበ ያለው በባለድርሻ አካላት ጥረት ስለሆነ ሊመሠገኑ ይገባል ብለዋል።
ምክትል አስተዳዳሪው አክለውም በተመዘገበው ውጤት የምንኩራራ ሳይሆን ቀጣይ ከሰራን በዕውቀትና በስነ-ምግባር የታነጸ ትውልድ ለማፍራት ጠቃሚ ፍንጭ አድርጎ መውሰድ ይገባል ብለዋል፡፡
በመድረኩ ለውይይት መነሻ የሚሆን ሰነድ የቀረበ ሲሆን የነበረው ጠንካራ አፈጻጸም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት፤ እንዲሁም በድክመት የመማሪያ መጽሐፍት አቅርቦት፣ የግል ትምህርት ቤቶች የቦታ ጥበት፣ አንዳንድ ትምህርት ቤቶች ከደረጃቸው በታች መሆናቸው የእርምት ስራና ክትትሎች መጠናከር እንደሚገባቸው ተነስቷል።
የጂንካ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቤቶች ርእሳነ መምህራን፣ ሱፐርባይዘሮች፣ የቀበሌ አመራሮችና የወላጅ ተማሪ መምህራን ህብረት ኮሚቴዎች ተገኝተዋል፡፡
ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ የ6ኛ፣ 8ኛ እና 12ኛ ክፍል ተማሪዎች የዋንጫ፣ መዳልያና የምስክር ወረቀት ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
ዘጋቢ፡ ጳውሎስ አሚገሮ – ከጂንካ ጣቢያችን
More Stories
የማታ 1፡00 ዜና 24፤ ሀዋሳ፡ ጥቅምት 04/2018 ዓ.ም
ጃፓን በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ብራዚልን አሸነፈች
ከተሞች በዲጂታል ቴክኖሎጂ ታግዘው አገልግሎት መሥጠታቸው የተገልጋይና የአገልጋይ ግንኙነት ጤናማና እርካታ የተሞላበት እንዲሆን የሚያስችል መሆኑ ተገለጸ