ከህዝብ ለሚነሱ የመሰረተ ልማት ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት የገቢ አሰባሰብ አቅምን ማሳደግ እንደሚገባ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ መስከረም 13/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) በየደረጃው ከህዝብ የሚነሱ የመሰረተ ልማት ጥያቄዎችን ደረጀ በደረጃ ምላሽ ለመስጠት የገቢ አሰባሰብ አቅምን ማሳደግ እንደሚገባ የጉራጌ ዞን ገቢዎች መምሪያ ገለፀ።

በዞኑ በተያዘው የ2018 በጀት ዓመት ከ4 ቢሊየን 244 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ተመላክቷል።

የጉራጌ ዞን ገቢዎች መምሪያ ኃላፊ አቶ ሚነወር ሃያቱ ከጣቢያችን ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለፁት፥ በዞኑ ህዝቡ የሚያነሳቸው የመሰረተ ልማት ጥያቄዎችን ደረጀ በደረጀ ምላሽ ለመስጠት የገቢ አቅምን ማሳደግ እንደሚገባ አስረድተዋል።

መምሪያው በ2017 በጀት ዓመት የተለያዩ የገቢ አርዕስቶችን በመለየት ለአካባቢ ልማቶች ማከናወኛ የሚሆን 3 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰብ መቻሉን ተናግረዋል።

በተያዘው የ2018 ዓ/ም በጀት ዓመት በሁሉም ዘርፍ ግብር የመሰብሰብ አቅምን በማሳደግ 4 ቢሊየን 244 ሚሊየን 384 ሺ 661 ብር ለመሰብሰብ አቅዶ እየሰራ እንደሆነ የገለፁት አቶ ሚኒወር፥ ለዚህ መሳካት ደግሞ ግብር ከፋዮች እና የባለሙያዎች ቅንጅትና ድጋፍ ማጠናከር እንደሚያስፈልግ አመላክተዋል።

አክለውም የመስቀል በኣልን ለማክበር ወደ ዞኑ የሚገቡ እንግዶች በዓሉን አክብረው ወደ መጡበት ስፍራ ከመመለሳቸው በፊት የአካባቢውን ልማት ለማፋጠን ከሚከናወኑ ተግባራት መካከል አንዱ የገጠር እርሻ መሬት ግብር በመሆኑ ለዚህ ተግባር ማስፈጸሚያ የሚሆነውን ገንዘብ አስቀምጠው አሊያም በህጉ መሠራት አሁን ከፍለው መሄድ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

በዚህ ወቅት በሚደረጉ ግብይቶች ሁሉ ደረሰኝ በመቁረጥ እና በመቀበል የግብይት ባህላችን በማሻሻል ህዝብ ለአካባቢ ልማት የራሳቸውን ሚና መጫወት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

በተለይ በዞኑ በዘንድሮ በጀት ዓመት የታክስ ስርዓቱን ለማዘመን በርካታ ስራዎችን እየተከናወኑ መሆኑን ገልፀው፥ ሁሉም ማህበረሰብ ግብሩን በአግባቡ በመክፈል ለዘርፉ ድጋፍ ማድረግ እንደሚጠበቅበት አመላክተዋል።

አያይዘውም የመስቀል በዓልን ተከትሎ በሚኖር ሰፊ ግብይት ነጋዴዎች ደረሰኝ በአግባቡ በመስጠት ከመንግስት የተጣለባቸውን አደራ በተገቢው እንዲወጡ እየተሰራ እንደሆነ የገለፁት አቶ ሚነወር፥ ታክስ በአሰራሩ መሠረት በመሰብሰብ ለአከባቢው ልማት እንደሚውል ገልጸዋል ።

መምሪያው የመስቀል በዓልን ምክንያት በማድረግ በዞኑ የተሻለ ገቢ ለመሰብሰብ በርካታ የሰው ሃይል በማሰማራት እየሰራ መሆኑን በማንሳት በዚህም በየቀኑ ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ ታክስ እየተሰበሰበ እንደሆነ ገልጸዋል።

በየደረጃው ያሉ የዞኑ መዋቅሮች ኢኮኖሚ ከሚያመነጨው ገቢ አሟጦ ለመሰብሰብ የሚያስችሉ ስልቶችን በመቀየስ አፈፃፀሙን በየጊዜው እየገመገሙ መሄድ እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል።

የመምሪያው ኃላፊ በመጨረሻም ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች በተለይም ለዞኑ ግብር ከፋዮች እንኳን ለመስቀል በዓል በሰላም አደረሳችሁ በማለት በዓሉ የሰላም፣ የፍቅር፣ የደስታና የብልጽግና እንዲሆንላቸው የመልካም ምኞት መልዕክት አስተላልፈዋል።

ዘጋቢ፡ ደጋጋ ሂሳቦ – ከወልቂጤ ጣቢያችን