የ“ጀወጀ” ባህላዊ ስርአት መስቀልን በጉጉት እንዲጠብቁት ከሚያደርጓቸው ሁነቶች መካከል አንዱ መሆኑ ተጠቆመ
የመጠያየቂያና የመከባበር ባህል መገለጫ የሆነውን “የጀወጀ” ባህላዊ ስርአት መስቀልን በጉጉት እንዲጠብቁት ከሚያደርጓቸው ሁነቶች መካከል አንዱ መሆኑን የጉመር ወረዳ ነዋሪዎች ገለጹ።
ይህ ባህላዊ እሴት እንደተጠበቀ ለትውልድ ሊሸጋገር እንደሚገባም ተመላክቷል።
በኢትዮጲያውያን ዘንድ ሃይማኖታዊ በአላትን ተከትለው የሚመጡ በርከት ያሉ ባህላዊ በአላት ያሉ ሲሆን ከነዚህ አንዱ በጉራጌ ብሄረሰብ በኩል የመስቀል በአል በዋለበት ሳምንት ጀምሮ የሚካሄደው “የጀወጀ” የተሰኘ የባልና ሚስት ቤተሰብ የሚጠይቅበት ፕሮግራም ነው።
በጉዳዩ ላይ ካነጋገርናቸው በጉራጌ ዞን ጉመር ወረዳ ነዋሪዎች መካከል አቶ ትእግስቱ ወልደጊዎርጊስ፣ ወ/ሪት አበበች ዘብሬ፣ አቶ ፈቀደ ገብሬና ወ/ሮ እየሩሳሌም ተሾመ በሰጡት አስተያየት፥ መስቀልን ከሚያስናፍቋቸው ክዋኔዎች መካከል የ“ጀወጀ” አንዱ መሆኑን ተናግረዋል።
ይህ ባህል ያገቡ ሴት ልጆች ከባለቤታቸው ጋር በመሆን ልጆቻቸውን ይዘው ወላጆቻቸውን የሚጠይቁበት ተጠባቂና ተናፋቂ ባህል ነው ባይ ናቸው።
በተለይም በአመቱ ውስጥ በተለያዩ አጋጣሚዎች የመገናኘት እድል የማይገጥማቸው የልጅት ቤተሰቦች የልጃቸውንና የልጅ ልጆቻቸውን ናፍቆት ለመወጣት ይህ ባህል ትልቅ እድል የሚፈጥላቸው መሆኑንም አክለዋል።
በሌላ በኩል ይላሉ ሃሳብ አጋሪዎቻችን፥ ይህ ባህል የመጠያየቂና የናፍቆት መወጣጫ ብቻም ሳይሆን ልጆች ለወላጆቻቸው ያላቸውን ትልቅ ክብርና ፍቅር የሚገልጡበት እንደሆነም ተናግረዋል።
ባልና ሚስት ታዲያ ልጆቻቸውን ይዘው ወደ ልጅት ቤት ሲያቀኑ ባዶ እጃቸው አይደለም፤ አቅም በፈቀደው መጠን ለመመረቂያ የሚሆን አንዳች ነገር ተይዞ ነው የሚኬደው።
የጉመር ወረዳ ባህል ቱሪዝም ፅ/ቤት ሃላፊ አቶ ሰብስቤ ፎንዣ በበኩላቸው መስቀል በጉራጌ መገለጫው ብዙ በመሆኑ ይህን ጠብቆ የማቆየት ስራ መሰራት ይኖርበታል ነው ያሉት።
በእርግጥ በማህበረሰቡ ከትውልድ ትውልድ ሲወራረድ የመጣውን ውብ ባህል እንዳስቀጠለው ጠቁመው፥ ፅ/ቤቱ ደግሞ ማህበረሰቡ ይህን ባህል ይበልጥ ጠብቆና ተንከባክቦ እንዲያስቀጥል በልዩ ልዩ መልኩ ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ እየሰራ ነው ብለዋል።
ዘጋቢ፡ ሚፍታ ጀማል – ከወልቂጤ ጣቢያችን

More Stories
የአርሶ አደሩን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ ከመቼውም ጊዜ በላይ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ተገለጸ
በግብርናው ዘርፍ የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ በትኩረት እንደሚሠራ በኮንታ ዞን የኤላ ሀንቻኖ ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት አስታወቀ
ለ20ኛ ጊዜ “ዲሞክራሲያዊ አንድነት፤ ለሀገራዊ መግባባት” በሚል መሪ ቃል የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል ለማክበር የጋሞ ዞን ም/ቤት የዝግጅት ሥልጠና እየሰጠ ነው