በልዩ ልዩ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር ወደ ትምህርት ገበታ ሊመጡ ያልቻሉ ተማሪዎች መደገፍ እንደሚገባ ተጠቆመ
ሀዋሳ፡ መስከረም 12/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) በልዩ ልዩ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር ሳቢያ ወደ ትምህርት ገበታ ሊመጡ ያልቻሉትን የመደገፍ ሥራ ከተለያዩ ረጂ አካላት ጋር በተቀናጀ ጥረት እየተሠራ እንደሚገኝ የዳዉሮ ዞን ትምህርት መምሪያ ገለጸ፡፡
በኒው ዳውሮ ፋውንዴሽን የበጎ አድራጊ ማኅበር በኩል የትምህርት ቁሳቁስ እጥረት ላለባቸው ለ500 ተማሪዎች የደብተርና የብዕር ድጋፍ ተደርጓል።
ላለፉት አራት ዓመታት በተከታታይ “አንድ እሽግ ለአንድ ልጅ” ዘመቻ በትምህርት ቁሳቁስ እጥረት መማር ያልቻሉ ወገኖችን የመርዳት ሥራዎች ሲሠሩ ቆይቷል።
በዚህ የድጋፍ ሂደት በርካቶች ወደ ትምህርት ገበታ ተመለሰው እየተማሩ መሆናቸውም ተጠቁሟል።
በ2018 የትምህርት ዘመን በሚደረገው የድጋፍ ተግባር ላይ የተገኘው የኒው ዳዉሮ ፋውንዴሽን መሥራች በኃይሉ ማቴዎስ እንደገለጹት፥ ይህ ድጋፍ በዳዉሮ ዞን ለአራተኛ ጊዜ የሚደረግ ሲሆን በማኅበራዊ የትስስር ገጽ በተሰበሰበው ገንዘብ እንደሆነም ነው የገለጹት።
ፋውንዴሽኑ አሁን ላይ በትምህርትና በሚዲያ ዘርፍ የጀመረውን ተግባር በቀጣይ በጤና፣ በውኃ ልማትና አረጋውያንን በመርዳት ሥራ ላይ የተሻለ ተግባር ለማከናወን ማቀዱንም ተናግሯል።
ባለፉት ሦስት ዓመታት ከ1 ሺህ 500 በላይ ለሚሆኑ ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ማቅረብ የተቻለ ሲሆን በተያዘው የትምህርት ዘመን ከ500 በላይ ለሚሆኑ ተማሪዎች በተገኘው ከ200 ሺህ ብር በላይ ገንዘብ ድጋፍ እንደሚደረግም ገልጿል።
እስካሁንም ፋውንዴሽኑ ከ800 ሺህ ብር በላይ በማኅበራዊ የትስስር ገጽ ባገኘው ገንዘብ የድጋፍ ሥራ መሥራቱንም አስረድቷል።
የዳዉሮ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ታማኝ ኃይሌ በበኩላቸው የበጎ አድራጎት ተግባራት በሁሉም የልማት ዘርፍ ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ለማስቻል በተቀናጀ ጥረት እየተሠራ እንዳለም ገልጸዋል።
ስለሆነም በኒው ዳዉሮ ፋውንዴሽን የተጀመረው መማር እየፈለጉ ግን በትምህርት ቁሳቁስ እጥረት የተቸገሩ ወገኖችን ለማስተማር እያደረገው የሚገኘው ጥረት የሚበረታታ መሆኑንም ገልጸዋል።
እንደ ዞን ከ211 ሺህ 642 ተማሪዎችን ለመቀበል የታቀደ ሲሆን እስካሁን 148 ሺህ ተማሪዎችን ብቻ የተመዘገቡ ሲሆን ከ60 ሺህ በላይ ሕጻናት ወደ ትምህርት ገበታ መቅረብ አለመቻላቸውን ተናግረዋል።
እንደምክንያት ከተጠቀሱት በዋናነት ምገባና የትምህርት ቁሳቁስ እጥረት በመሆኑ በቀጣይ በተቀናጀ ጥረት ሕጻናትን ወደ ትምህርት ገበታ ማምጣትና ማቆየት ወሳኝ በመሆኑ የጋራ ጥረት እንደሚደረግም ገልጸዋል።
በድጋፉ የተገኙ ቤተሰቦችና ተጋባዥ እንግዶች በሰጡት አስተያየት ላለፉት ሦስት ዓመታት በተከናወኑ ተግባራት ውጤት መመዝገቡ አስደስቷቸዋል።
በድጋፍና ለአንድ እሽግ ለአንድ ልጅ ዘመቻ መዝጊያ ፕሮግራም ላይ ድጋፍ የሚደረግላቸው ተማሪዎችና ወላጆች በየደረጃው የሚገኙ የዞኑንና የታርጫ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ የሥራ ኃላፊዎች በዕለቱ ተገኝተዋል።
ዘጋቢ፡ መሣይ መሠለ – ከዋካ ጣቢያችን
More Stories
በያሆዴ በዓል ወቅት የሚደረገው ሲምፖዚየም ለሀገር ልማትና አንድነት ያለው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑ ተገለጸ
ጥራትና ወቅታዊነት ላይ ትኩረት ያደረገ የዕቅድ ዝግጅት አስፈላጊ መሆኑ ተገለጸ
6111 ok ለአርባ ምንጭ ስታድየም ግንባታ ባለ አራት ዲጅት የገቢ ማሰባሰቢያ ቁጥር ይፋ ተደረገ