ጥራትና ወቅታዊነት ላይ ትኩረት ያደረገ የዕቅድ ዝግጅት አስፈላጊ መሆኑ ተገለጸ

ጥራትና ወቅታዊነት ላይ ትኩረት ያደረገ የዕቅድ ዝግጅት አስፈላጊ መሆኑ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ መስከረም 12/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) በዕቅድ ዝግጅት ወቅት ጥራትና ወቅታዊነት ላይ ትኩረት ሊደረግ እንደሚገባ የኮሬ ዞን አስተዳደር አሳሰበ፡፡

በኮሬ ዞን ፕላንና ልማት ዩኒት በአንድ ዕቅድና አንድ ሪፖርት አዘገጃጀትና በ2017 ዓ/ም ዞናዊ አፈጻጸም ላይ ያተኮረ የግንዛቤ ማስጨበጫ ውይይት ተካሂዷል፡፡

የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኮሬ ዞን አስተዳደር ተወካይ የሆኑት አቶ አብዱርቃድር ኡስማን፥ በየተቋማቱ በዕቅድና ሪፖርት አዘገጃጀት ላይ የነበሩ ችግሮች ቀስበቀስ እየተፈቱ ናቸው ብለዋል።

ዕቅድ ከሌለ ተግባር እንደማይኖር ያነሱት አቶ አብዱልቃድር፥ የሚዘጋጁ ዕቅዶች ጥራትና ወቅታዊነት ትኩረት ሊደረግባቸው ይገባል ሲሉ ተናግረዋል ።

የኮሬ ዞን ፕላንና ልማት ዩኒት አስተባባሪ አቶ አስማማው አየለ፥ የዕቅድ አዘገጃጀትና አተገባበር ላይ ቀድሞ የነበረንን ዕውቀት እያዳበርን ለሚቀጥለው ደግሞ በትጋት ለመስራት ታልሞ የተዘጋጀ መድረክ እንደሆነ ገልጸዋል ።

ዕቅዶች ሲዘጋጁ ጊዜና ወቅታቸውን የጠበቁ፣ ተዓማኒነት ያሏቸውና ግልጽ የሆኑ መሆን አለባቸው ብለዋል።

በዕቅድ አዘገጃጀትና ትግብራ በ2017 ዓ/ም አፈጻጸም ላይ የነበሩ ጠንካራና ደካማ ጎኖች ላይ ያተኮረ ሰነድ ለተሳታፊዎች ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል ።

የተቋማት ዕቅድ አዘገጃጀት፣ የካፒታል ፕሮጀክቶች አፈጻጸም፣ የሶሺዮ ኢኮኖሚያዊ መረጃዎች አያያዝና ያለንን ሀብት በሚገባ ከመጠቀም አኳያ ያሉ ውስንነቶች መቀረፍ እንዳለባቸው በመድረኩ ትኩረት የተሰጣቸው ጉዳዮች ነበሩ።

የመድረኩ ተሳታፊዎችም በአንዳንድ ሴክተሮች ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን በትኩረት ለመፍታትና በዕቅድ ዝግጅትና ትግበራ ላይ ጥሩ ግንዛቤ እንድናገኝ ያስቻለ መድረክ ነው ብለዋል።

ሁሉም ባለድርሻ አካላት ኃላፊነት በመውሰድ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ከመሙላት ረገድ በቁርጠኝነት መስራት እንዳለባቸው ተሳታፊዎቹ ገልጸዋል።

ዘጋቢ: ለምለም ኦርሳ – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን