ከመስቀል በዓል ጋር ተያይዞ በመሠረታዊ የፍጆታ ዕቃዎችና ሸቀጣሸቀጦች ላይ ህገ-ወጥ የዋጋ ጭማሪ እንዳይኖር ከመቼውም ጊዜ በላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ
ሀዋሳ፡ መስከረም 11/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) በምስራቅ ጉራጌ ዞን ከመስቀል በዓል ጋር ተያይዞ በመሠረታዊ የፍጆታ ዕቃዎችና ሸቀጣሸቀጦች ላይ ህገ-ወጥ የዋጋ ጭማሪ እንዳይኖር ከመቼውም ጊዜ በላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑ የዞኑ ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ አስታወቀ፡፡
የምስራቅ ጉራጌ ዞን ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ኃላፊ ወ/ሮ ቤተልሄም ታደሰ እንደገለፁት በመስቀል በዓል ወቅት ለበዓል ፍጆታ የሚውሉ ሸቀጦች እና ሌሎች ግብይቶች ከሌሎች ጊዜያት በተለየ ትኩረት የሚከናወንበት ወቅት በመሆኑ ህገ-ወጥ የዋጋ ጭማሪ እንዳይኖር ከመቼውም ጊዜ በላይ ታቅዶ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተሰራ ነው።
በ2018 ዓ/ም የዘመን መለወጫ በዓልን በማስመልከት ህገ ወጥ የዋጋ ጭማሪ እንዳይኖር በቅንጅት በመሰራቱ አበረታች ውጤት መመዝገቡን ጠቁመው፥ የመስቀል በዓልን ምክንያት በማድረግ ገበያውን ለማረጋጋት በሰንበት ገበያዎችና በሌሎችም ግብረ-ኃይል ተቋቁሞ ከባለድርሻ አካላት በመቀናጀት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በዞኑ ዘወትር የንግድ ሂደቱን ክትትልና ቁጥጥር የማድረግ፣ አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪ እንዳይደረግና ያለደረሰኝ ግብይት እንዳይፈፀም በአጽንኦት እየተሰራ መሆኑን አመላክተዋል።
የመምሪያ ሀላፊዋ ወ/ሮ ቤተልሔም ታደሰ የበዓል ገበያን ለማረጋጋት በ13 የሰንበት ገበያ ማዕከላት ላይ የምርት እጥረት እንዳይኖር እየተሰራ መሆኑን አስረድተው፥ ከነዚህም አስሩ የሰንበት ገበያ ማዕከላት ሳምንቱን ሙሉ አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኙ አመላክተዋል።
በሁሉም አካባቢዎች ህገ-ወጥ የንግድ እንቅስቃሴና ምርት መደበቅ እንዳይኖር እንዲሁም ምርቶች በግብይት ሥርዓት እንዲመሩ እንደ ዞን የተቋቋመው ግብረ-ኃይል በቀጣይነት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሆነ የጠቆሙት ኃላፊዋ፥ መምሪያው ለዘርፉ ውጤታማነት በየደረጃው እያደረገ የሚገኘውን ጥረት ሁሉም ማገዝ እንዳለበት ጥሪ አቅርበዋል።
የቡታጅራ ከተማ አስተዳደር ንግድና ገበያ ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ ተስፋዬ አህመድ በበኩላቸው በከተማው በተለይም የመስቀል በዓልን ምክንያት በማድረግ የንግድ ስርዓቱ ጤናማ እንዲሆንና አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪ እንዳይኖር ግብረ ሀይል በማቋቋም በቅንጅት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
በከተማው የሚገኝ ትልቅ የአርብ ገበያን ጨምሮ በተቋቋሙ የሰንበት ገበያዎች በመታገዝ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ሰፊ የምርት አቅርቦት እንዲኖር መሰራቱን በማንሳት ተገቢነት የሌለው የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ አካላት ላይ ህጋዊ እና አስተዳደራዊ እርምጃ እንደሚወሰድ አበክረው ተናግረዋል።
በከተማው ከሰንበት አስከ ሰንበት የግብይት አገልግሎት የሚሰጡ የገበያ ማዕከላት መቋቋማቸውን ያስረዱት ሀላፊው በዚህም ሸማቹ ህብረተሰብ የሚፈልገውን ግብአት በተመጣጣኝ ዋጋና በአቅራቢያው በቀላሉ እንዲያገኝ ዕድል ተፈጥሮለታል ነው ያሉት።
ጽ/ቤቱ በዘርፉ የጀመረውን ስራ ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ ትርጉም ባለው መልኩ እየሠራ እንደሚገኝ ጠቁመው ለዘርፉ ስኬታማነት በየደረጃው በሚደረገው እንቅስቃሴ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የድርሻውን እንዲወጡ ሀላፊው መልዕክት አስተላልፈዋል።
በቡታጅራ ከተማ ሲገበያዩ አግኝተን ካነጋገርናቸው ሸማቾች መካከል በሰጡት አስተያየት ለመስቀል በዓል የሚያስፈልጓቸውን የፍጆታ ዕቃዎችን በተሻለ ጥራትና በተመጣጠኝ ዋጋ መግዛታቸውን ተናግረዋል፡፡
በከተማው የሰንበት ገበያዎችን ጨምሮ ሌሎች የገበያ አማራጮች መስፋታቸው የምንፈልገውን ዕቃ መርጠን በተሻለ ዋጋ ለመግዛት አስችሎናል ሲሉ ነው የገለፁት፡፡
በከተማው አሁን ላይ አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪ እንዳይኖር እየተደረገ ያለውን ጥረት አድንቀው በቀጣይም ይህንኑ በጎ ተግባር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
ሸማቹ ህብረተሰብ ከአላስፈላጊ ወጪ እራሱን እንዲጠብቅና ገቢንና አቅምን ባማከለ መልኩ በዓሉን ማሳለፍ እንዳለበትም አስተያየታቸውን አክለዋል።
ዘጋቢ፡ መሀመድ ሽሁር – ከወልቂጤ ጣቢያችን
More Stories
የማታ 1፡00 ዜና 24፤ ሀዋሳ፡ ጥቅምት 04/2018 ዓ.ም
ጃፓን በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ብራዚልን አሸነፈች
ከተሞች በዲጂታል ቴክኖሎጂ ታግዘው አገልግሎት መሥጠታቸው የተገልጋይና የአገልጋይ ግንኙነት ጤናማና እርካታ የተሞላበት እንዲሆን የሚያስችል መሆኑ ተገለጸ