መልካም እሴቶችን በማልማት ማሳደግና ማስተዋወቅ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ነው – ሚኒስትር ዴኤታ ነፊሳ አልመሃዲ
ሀዋሳ፡ መስከረም 11/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) መልካም እሴቶችን በማልማት ማሳደግና ማስተዋወቅ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ነው ሲሉ በኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የባህልና ቋንቋ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ነፊሳ አልመሃዲ ገለፁ።
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጠምባሮ ልዩ ወረዳ የብሔረሰቡ ባህል፣ ቋንቋና ታሪክ ልማት ሲምፖዚየም በልዩ ወረዳው ሙዱላ ከተማ ሲካሔድ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት፥ በኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የባህልና ቋንቋ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ነፊሳ አልመሃዲ፥ “ሀገራችን ኢትዮጵያ የሰው ልጅ መገኛ የድንቅ ታሪካዊ እሴቶች ባለቤት ናት ብለዋል።
የህዝቦች አንድነት ለዘላቂ ልማት” በሚል መሪ ቃል የሚከበረው የጠምባሮ ባህል፣ቋንቋና ታሪክ ስምፖዚየም ከነዚያ አንዱ መሆኑን አመላክተው፥ ይህንና ሌሎችን ባህላዊና ታሪካዊ እሴቶችን ብሎም ቋንቋዎችን ለማሳደግ ሚኒስትር መስሪያ ቤቱ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።
ሚኒስትር መስሪያ ቤቱ የጠምባሮን ቋንቋ ለማሳደግ የሚሰራው ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመው ታሪካዊና ባህላዊ እሴቶችን ጠብቆ ለትውልድ ለማሻገር በቅንጅት ሊሰራ እንደሚገባ አመላክተዋል።
በሲምፖዚየሙ የተገኙት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈጉባኤ መነቴ ሙንዲኖ፥ ጠምባሮ ውብ የተፈጥሮ ፀጋዎቹን ለቱሪዝም ምቹ በማድረግ የማልማት ተግባር ትልቅ ትኩረት የሚሻ መሆኑን ጠቁመው፥ ሁላችንም እንደ ጠምባሮ ሁሉ ሀገራዊ ባህላዊ እሴቶቻችንን የመጠበቁን ኃላፊነት በጋራ ልንወስድ ይገባል ብለዋል።
ኢንጂነር ሀብታሙ በላይነህ የጠምባሮ ልዩ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ የጠምባሮ ብሔረሰብ የራሱ ወሰን ያለው ባህሉንና ማንነቱን ጠብቆ የኖረ የበርካታ ባህላዊ እሴቶች ባለቤት ነው ብለዋል።
መሳላ(መሪሾ)ያለው ለሌለው በማካፈል የጋራ አንድነትን በማጉላት የሚከበር በዓል እንደመሆኑ ባህሉንና ትውፊቱን ጠብቆ ማቆየት እንደሚገባ በመጠቆም አንድነትን የሚሸረሽሩ እኩይ ተግባራትን በጋራ በመመከት ለጋራ ሀገራዊ ሠላም በቅንጅት ሊሰራ እንደሚገባ አመላክተዋል።
ዘጋቢ: አማኑኤል አጤቦ – ከሆሳዕና ጣቢያችን
More Stories
የማታ 1፡00 ዜና 24፤ ሀዋሳ፡ ጥቅምት 04/2018 ዓ.ም
ጃፓን በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ብራዚልን አሸነፈች
ከተሞች በዲጂታል ቴክኖሎጂ ታግዘው አገልግሎት መሥጠታቸው የተገልጋይና የአገልጋይ ግንኙነት ጤናማና እርካታ የተሞላበት እንዲሆን የሚያስችል መሆኑ ተገለጸ