“ያለ ውጣ ውረድ የሚገኝ ስኬት የለም” – ወጣት አሰለፈች ሌንጫ

“ያለ ውጣ ውረድ የሚገኝ ስኬት የለም” – ወጣት አሰለፈች ሌንጫ

በሊዲያ ታከለ

በኢትዮጵያ ለአካል ጉዳተኞች የሚመቹ መሰረተ ልማቶች በበቂ ሁኔታ አለመሰራታቸው እና የአገልግሎት አሰጣጥ ጉድለቶች መኖራቸው አካል ጉዳተኞችን ለከፍተኛ እንግልት እና የጤና ችግሮች እየዳረጋቸው ስለመሆኑ እሙን ነው። የህብረተሰቡ ግንዛቤ ማነስ ደግሞ ለዚህ በምክንያትነት ይጠቀሳል፡፡

አሁን አሁን እየተሻሻሉ ያሉ ጉዳዮች ቢኖሩም የበለጠ መሰራት እንዳሚገባ አካል ጉዳተኞች ከሚገጥሟቸው ችግር በመነሳት መናገር ይቻላል፡፡

የክረምቱ ጊዜ ዲቾች በጎርፍ የሚሞሉበት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የተለየ ትኩረት በመስጠት መንገዶችን አመቺ በሆነ መልኩ መገንባት፣ ከዚህ ባለፈ ሕንጻዎችና ሌሎች ግንባታዎች አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያደረጉ እንዲሆን ማመቻቸት ያስፈልጋል፡፡

ከማሳሰቢያው አለፍ ስንል፣ በሕይወታቸው የሚገጥማቸውን ውጣ ውረድ በትዕግስት አልፈው ለቁምነገር የበቁ በርካታ አካል ጉዳተኞችን እናገኛለን፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ለሚገጥሟት ፈተናዎች እጅ ሳትሰጥ እራስዋን ለመቀየር ስለምትጥር አንዲት ወጣት እንተርክላችሁ፡፡

ወጣቷ አሰለፈች ሌንጫ ትባላለች። ተወልዳ ያደገችው በወላይታ ሶዶ ጊሎ ቢሳሬ በምትባል ትንሽዬ የገጠር መንደር ውስጥ ነው፡፡ ቤተሰቦቿ በግብርና ስራ ነው የሚተዳደሩት፡፡

ወጣቷ ስትወለድ ምንም የአካል ጉዳት አልነበረባትም፡፡ አራት ዓመት ሲሞላት ግን ለቤተሰቦቿ ከባድ ሀዘንን የፈጠረ ክስተት መጣ፡፡

ይኸውም የአጎቷ ህልፈት ነበር፡፡ በወቅቱ እናቷ ሃዘን ሊደርሱ የሚመጡ እንግዶች በብዛት ስለነበሩ እሷን ከታላቅ ወንድሟ ጋር ወደ ጎረቤት ቤት በመውሰድ አስቀመጧት። እሷም የልጅነት ነገር ሆኖ የተቀመጠችበት ቤት ውስጥ ራሷን በጨዋታ ወጠረች። በጨዋታ መሃልም አልጋ ላይ ወጣች፡፡ ይሁን እንጂ ይህ አጋጣሚ ለአካል ጉዳት ዳረጋት፡፡

በወቅቱ በገጠር የጠፈር አልጋ የሚባል የሌሊት ማረፊያ ነበር፡፡ በጨዋታ መሃል ድንገት እግሯ አልጋው ውስጥ ሾልኮ ተቀረቀረ። አብሯት ይጫወት የነበረው ወንድሟ እና እሷ እግሯን ከተቀረቀረበት ለማውጣት መጎተት ጀመሩ፡፡

ሰው በመጥራት ፈንታ እግሯን ለማውጣት ሁለቱም ያደርጉት በነበረው ጥረት የጉልበቷ አጥንት ተሰበረ፡፡ ወላጆቿ የእግሯን ጉዳት ወደነበረበት ለመመለስ የተቻላቸውን ሁሉ አደረጉ፡፡ አልተሳካም፡፡

ወደ ባህል ህክምና ወይም ወጌሻ በመውሰድ የእግሯን ጉዳት ለማስታረቅ ብዙ ለፉ፡፡ ሆኖም ግን ውጤቱ እንደተፈለገው ሊሆን አልቻለም፡፡

ብቸኛው አማራጭ ያጋጠማትን ችግር አምኖ መቀበል ሆነ፡፡ ቤተሰቦቿም በአካል ጉዳተኝነቷ ምክንያት አሉታዊ ስሜት እዳይሰማት የተቻላቸውን ሁሉ ያደርጉላት ነበር፡፡

በልጅነት አዕምሮዋ መሸከም የማትችለውን ነገር ለመሸከም ተገደደች። እድሜዋ ለትምህርት ሲደርስ ግን በዚያው በትውልድ ቀዬዋ በሚገኘው ጊሎ ቢሳሬ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤትን ተቀላቀለች፡፡ ወደ ትምህርት ቤት ስትሄድም ሆነ ስትመለስ በዱላ ተደግፋ ነበር፡፡

በወቅቱ እህቷ አብራት ስለምትማር ደብተሯን በመያዝ ታግዛት ነበር፡፡ እንኳን መንገዱ ወጣ ገባ መሆኑ ለጉዞዋ አስቸጋሪ ቢሆንባትም የሰው ጥገኛ መሆን አልፈለገችም። በምርኩዝ እየታገዘች ደርሶ ለመመለስ ታገለች፡፡

የአምስተኛ ክፍል ተማሪ እያለችም ህመም አጋጠማትና ትምህርቷን እንድታቆም ጫና ፈጠረባት፡፡ ይሁን እንጂ የደረጃ ተማሪ በመሆኗና ለትምህርቷ ባላት ትልቅ ፍቅር ምክንያት የገጠማትን ጫና ተቋቁማ ለመማር ያልፈነቀለችው ድንጋይ አልነበረም፡፡

ጥረቷም መና ሆኖ አልቀረም፡፡ አራት ወራትን በህመም ካሳለፈች በኋላ ወደ ትምህርት ገበታዋ ተመልሳ መማሯን ቀጠለች።

ስምንተኛ ክፍል ስትደርስ ሚንስትሪ ተፈትና ውጤት ብታመጣም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በአቅራቢያቸው ባለመኖሩ ሌላ ፈተና ተጋረጠባት፡፡

ሆኖም ወላጆቿ ከእርሷ ጋር ተማከሩ። ከምክክሩና መግባባቱ በኋላ የተወሰነ ጥሪታቸውን ሽጠው ከወንድሞቿ ጋር እንድትማር ወደ ወላይታ ሶዶ ላኳት፡፡

እዚያም ትምህርቷን በምትከታተልበት ወቅት ሌላ ፈተና አጋጠማት፡፡ የአስረኛ ክፍል ማትሪክ ፈተና ልትፈተን ጥቂት ወራት ሲቀራት በድጋሚ ታመመች፡፡

መምህሮቹ የገጠማትን ህመም ምክንያት አድርገው በቀጣዩ ዓመት እንድትፈተን ቢጎተጉቷትም እሷ ግን ትምህርቷን ለማቋረጥ ፈቃደኛ አልሆነችም፡፡ በሃሳቧ ጸንታም የማትሪክ ፈተና ተፈተነች፡፡ ውጤቱ እንደጠበቀችው ባለመሆኑ ከባድ ሀዘን ተሰማት፡፡

ይህ በእንዲህ እያለ መልካም ዜና ተሰማ፡፡ በአካል ጉዳተኞች ዙሪያ የሚሰራ በጎ አድራጎት ድርጅት ወደ ሀዋሳ ሄዳ የትምህርት እድል የምታገኝበትን አጋጣሚ እንዳመቻቸላት እና ከእሷ ጋር ሌሎች ሶስት ልጆችም እድሉን እንዳገኙ አበሰራት፡፡

ባገኘችው እድል ከፍተኛ ደስታ ተሰማት። ወላጆቿም ይህንን ዜና ሲሰሙ ደስታቸው ወደር አልነበረውም፡፡ ሆኖም ግን ድርጅቱ 3 ሺህ ብር ጠየቃት። ይሄኔ ወላጆቿ ካላቸው የእርሻ መሬት የተወሰነውን በረጅም ጊዜ ኪራይ አከራይተው ባገኙት ገንዘብ ወደ ሀዋሳ ከተማ እንድታቀና መንገዱን አመቻቹላት፡፡ ወደ ሀዋሳ መጣች፡፡

በወቅቱ የገጠማትንም አሰለፈች እንዲህ ስትል ታስታውሳለች፡-

“ወደ ሀዋሳ እንድንመጣ የጎተጎተን ድርጅት ወደ ከተማዋ ከመጣን በኋላ ድጋሚ አላገኘንም፡፡ ከእኔ ጋር ከመጡት ሁለቱ ልጆች ወደ መጡበት ተመለሱ፡፡ ምክንያቱም ወላጆቻቸው እነሱን ማገዝ ሳይችሉ ቀሩ፡፡

“እኔም ለወላጆቼ የሆነውን ነገር ሳስረዳቸው አባቴ በፍጹም መመለስ እንደሌለብኝና እኔን ለማስተማር አስፈላጊውን መስዋዕትነት እንደሚከፍልልኝ ነገረኝ፡፡ ከዚያም በሀዋሳ ፖሊ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ የቴክስታይል ኬሚካል የትምህርት ክፍል ገብቼ ተማርኩኝ፡፡

“የብቃት ማረጋገጫ ፈተና ከወሰድኩ በኋላም ወላጆቼን ማስቸገር እንደሌለብኝና እራሴን ማስተዳደርና እንዳለብኝ ተረዳሁ። ሀዋሳ ኢንዱስትሪያል ፓርክ ውስጥ ስራ ጀመርኩ፡፡

“በፓርኩ ስራ የጀመርኩት ግን በጨርቃ ጨርቅ ስፌት ነበር፡፡ ይህ ደግሞ ለእኔ ከባድ ነበር፡፡ ስራውን እንዲቀይሩልኝ ካልሆነ ግን ስራውን እንደምለቅ አሳወቅኳቸው፡፡ የተወሰነ ከተነጋገርን በኋላ ጉዳቴን ተረድተው ወደ ሌላ ክፍል ቀየሩኝ፡፡

“አሁን ለእኔ በሚመች የሥራ ክፍል ውስጥ ክፍል እየሰራሁ እገኛለሁ፡፡ ብዙም ጫና አይበዛብኝም፡፡ ተቀምጬ ስለምሰራ የሚያስቸግረኝ ነገር የለም፡፡ በስራዬም ደስተኛ ነኝ፡፡”

በርካታ የሕይወት ውጣ ውረዶችን አልፋ አሁን የደረሰችበት ደረጃ ላይ የተገኘችው ወጣት አሰለፈች ሌንጫ የሕይወት ልምዶቿን መነሻ በማድረግ ሌሎችን እንዲህ በማለት ትመክራለች፡-

“በሕይወታችን የሚገጥሙንን ትግሎች በማለፍ ካሰብንበት መድረስ እንችላለን፡፡ በእርግጥ መንገዱ አልጋ በአልጋ አይሆንም። ይሄንን ካወቅን ፈተናዎች ከመንገዳችን ሊያሰቀሩን አይገባም፡፡ ያለውጣ ውረድ የሚገኝ ስኬት የለም፡፡ ሁሉም ነገር የስኬት መንገድ ጥረትና ትዕግስት የሚጠይቅ ነው። ስለዚህ ማለፍ የሚገቡንን ፈተናዎች በትዕግስት በማለፍ ለስኬት መብቃት እንችላለን፡፡”