ከዚህ ቀደም ከባንኩ የብድር አገልግሎት ያገኙ ግለሰቦችም ሆኑ ማህበራት እስከ ሰኔ 23/2015 ዓ.ም ድረስ የወሰዱትን ብድር የሚመልሱ ከሆነ ከቅጣት ነጻ እንደሚሆኑ ተገለጸ
ሀዋሳ፡ ሰኔ 10/2015 ዓ.ም (ደሬቴድ) ከዚህ ቀደም ከባንኩ የብድር አገልግሎት ያገኙ ግለሰቦችም ሆኑ ማህበራት እስከ ሰኔ 23/2015 ዓ.ም ድረስ የወሰዱትን ብድር የሚመልሱ ከሆነ ከቅጣት ነጻ እንደሚሆኑ የኦሞ ባንክ ቦንጋ ዲስትሪክት አስታወቀ።
የአሰራር ስርዓቱን በማሻሻል የአነስተኛ ብድር እና ቁጠባ አገልግሎቶችን ከባንክ ሥራ ጋር በማጣመር እያከናወነ እንደሚገኝ ተገልጿል።
ባንኩ ከዚህ ቀደም የማይክሮ ፋይናንስ አገልግሎት አየሰጠ ባለበት ወቅት ከፍተኛ ብድሮችን መውሰድ የማይችሉና በአነስተኛ የኑሮ ደረጃ ያሉ የህብረተሰብ ክፍሎች አገልግሎቱን በአግባቡ ማግኘት እንዲችሉ ብብዙ መልኩ ሲሰራ መቆየቱን የዲስትሪክቱ ስራ አስኪያጅ አቶ አስራት ኋይሌ ተናግረዋል።
አሁንም ደንበኞች ይህንኑ አገልግሎት እንዲያገኙ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን የገለፁት ስራ አስኪያጁ በካፋ ዞን በ16 ቅርንጫፎች በገጠር እና በከተማ ግብርና፣ በጥቃቅን እና አነስተኛ እንዲሁም በሌሎች የሥራ መስኮች ለተሰማሩ የህብሰተሰብ ክፍሎች የብድር አገልግሎት በመስጠት ደንበኞች ኑሮአቸውን እንዲያሻሽሉ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።
በዚህም በካፋ ዞን እስካሁን ከ 1 መቶ 78 ሺ በላይ ለሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ የብድር አገልግሎት ተደራሽ የተደረገ ሲሆን ከዚህም ማስመለስ የተቻለው 1 ነጥብ 6 ቢሊዮን 7 መቶ 21 ሺ ብር ያህሉን ነው ብለዋል።
የተቀረውን የብድር ገንዘብ ለማስመለስ ከተለያዪ አካላት ጋር እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ መሆኑን የገለጹት አቶ አስራት ብድር ወስደው በወቅቱ ያልመለሱ ደንበኞች እስከ ሰኔ 23 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ የሚመልሱ ከሆነ ከቅጣት ነጻ እንደሚሆኑ ተናግረዋል።
ስለሆነም በተቀሩት ቀናት ደንበኞች የወሰዱትን ገንዘብ ተመላሽ በማድረግ የባንኩን የቀጣይ እቅድ ውጤታማ ለማድረግ የበኩላቸውን እንዲወጡ አቶ አስራት ጥሪ አስተላልፈዋል።
ዘጋቢ: ትዕግስቱ ጴጥሮስ – ከቦንጋ ጣቢያችን
More Stories
በከተሞች የሚስተዋሉትን የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለመፍታት ለሚደረገው ጥረት ህብረተሰቡ ሰፊ ድርሻ እንዳለው ተገለጸ
ማህበራዊ ሚዲያን በአግባቡ በመምራት እና በመጠቀም የአካባቢን ገጽታ መገንባት እንደሚገባ ተጠቆመ
የአዳሪ ትምህርት ቤቶች መስፋፋት ጥራት ያለው ተወዳዳሪ ዜጋ ለማፍራት እንደሚያስችል ተገለጸ