አስፈፃሚ መሥሪያ ቤቶች ወቅቱን የሚመጥን አገልግሎት ለህዝቡ መስጠት እንዳለባቸው ተገለጸ

አስፈፃሚ መሥሪያ ቤቶች ወቅቱን የሚመጥን አገልግሎት ለህዝቡ መስጠት እንዳለባቸው ተገለጸ

ሀዋሳ፡ ሰኔ 09/2015 ዓ.ም (ደሬቴድ) አስፈፃሚ መሥሪያ ቤቶች ወቅቱን የሚመጥን አገልግሎት ለህዝቡ መስጠት እንዳለባቸው የደቡብ ኦሞ ዞን ምክር ቤት አሳሰበ።

የምክር ቤቱ ዋና አፈ ጉባኤን ጨምሮ የሦስቱም ዘርፍ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎችና አባላት በደቡብ ኦሞ ዞን ደቡብ አሪ ወረዳ የተለያዩ ልማታዊ ሥራዎችን መስክ ምልከታ አድርገዋል።

ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ መስጠት የሚችል ሰፊ የችግኝ ጣቢያ ላይ ያለው ተግባር በቀጣይ እንደሀገር የተጀመረውን አረንጓዴ ልማት ከማረጋገጥ ባለፈ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርትን በአካባቢው በስፋት ለማልማት ትልቅ አስተዋጽኦ ሊያበረክት እንደሚችል በመስክ ምልከታው ማረጋገጥ ተችሏል።

የተጀመሩ የጋዘር ከተማ ውስጥ ውስጥ መንገድ ሥራ፣ በሴቶች ዘርፍ ያሉ ተግባራት ውስን ቢሆኑም በበጎ ጎን በምክር ቤቱ ዋና አፈ ጉባዔና ቋሚ ኮሚቴ ተወስዷል።

በአንፃሩ የጋዘር ፖሊስ ጣቢያ ህንፃ እየፈረሰና ከአገልግሎት ውጭ እየሆነ በመሆኑ ፈጣን ምላሽ እንደሚያስፈልግ፣ በተቋሙ ውስጥ ለተጠርጣሪ ግለሰቦች በቂ ማረፊያ አለመኖር እና አጠቃላይ የፍትህ ሥርዓቱ በቅንጅት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት መሠራት እንዳለበት ህግና ፍትህ መልካም አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ዱንጋ ናኩዋ አሳስበዋል።

የመንግስት ሀብት ሆኖ በየዓመቱ እየተንከባለለ ከወረዳው በጀት የሚቆረጠው የማዳበሪያ ዕዳ፣ የወረዳው ምክር ቤት አዳራሽ ህንፃ ግንባታ መጓተትና ጥራት ማነስ ትኩረት ተሰጥቶ ምላሽ ሊያገኝ ይገባል ተብሏል።

በፍሕ ሥርዓቱ ዙሪያ ለሕዝቡ ቀጣይነት ያለው ግንዛቤ መስጠት እንደሚያስፈልግም ተመላክቷል።

አካል ጉዳተኞችና አረጋዊያን የልማት ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ የዞኑ ምክር ቤት ማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ ታሪኳ ደምሴ አሳስበዋል።

በሴቶች ሁለንተናዊ ለውጥ ዙሪያም ድጋፍ እንደሚያሻና ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጥ ያስፈልጋል ተብሏል።

የወረዳው ገቢ በጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የኢኮኖሚ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ ወግነሽ ፊንሳ ገልፀው ተጨማሪ ከዕቅድ በላይ በማሳካት ልማታዊ ሥራዎችን ማሳለጥ ያስፈልጋል ብለዋል።

የኦዲት ግኝቶችን ማስመለስ የተጠሪ አስፈፃሚ መሥሪያ ቤቶች ሀላፊነት በመሆኑ በአግባቡ መሠራት አለበት ተብሏል።

የመሬት ወረራና ህገወጥ ግንባታ ዙሪያ ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበትም ተመላክቷል።

በመስክ ምልከታ በጥንካሬ የታዩ ጎልብተው፤ በውስንነት የተመዘገቡ ደግሞ በዕቅድ ተካተው ፈጣን ምላሽ መሰጠት እንዳለበት ለአስፈፃሚ መሥሪያ ቤቶች ግብረ መልስ መሰጠቱን የተናገሩት የደቡብ ኦሞ ዞን ዋና አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ስመኝ ናቸው፡፡

ዘጋቢ: ተመስገን አበራ – ከጂንካ ጣቢያችን