በመኸር አዝመራ ከ400 ሺህ ሄክታር በላይ ማሳ በማልማት ከ17 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት እየተሰራ ነው – አቶ ማስረሻ በላቸው
ሀዋሳ፡ ነሐሴ 22/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በመኸር አዝመራ ከ400 ሺህ ሄክታር በላይ ማሳ በማልማት ከ17 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት እየተሰራ መሆኑን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው ገለጹ፡፡
በክልሉ በካፋ ዞን የአዲዮ እና በቤንች ሸኮ ዞን የጉራፈርዳ ወረዳ አርሶ አደሮች ለተሻለ ውጤት እየተጉ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው፤ በዋና ዋና ሰብሎች ከ356 ሺህ ሄክታር በላይ ማሳ በማልማት ወደ 8.3 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት እቅድ መያዙን ተናግረዋል።
በሆርቲካልቸር ተክሎችም እንዲሁ ከ45 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ በማልማት ወደ 9.1 ሚሊዮን ኩንታል ምርት እንደሚገኝ አስረድተዋል።
በጥቅሉ ወደ 17.5 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።
በመኸር አዝመራ ከ348 ሺህ ሄክታር በላይ የሚሆን ማሳ ለሰብል የተዘጋጀ ሲሆን ከ248 ሺህ ሄክታር በላዩ በዘር መሸፈኑን ጠቁመዋል።
ይህም የአቅዱ 69.5 በመቶ እንደሆነ አስረድተው፤ በቀረው ጊዜ የአዝመራውን እቅድ ለማሳካት እንደሚሰራ አስረድተዋል።
ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ከሚሰሩ ስራዎች መካከል ዋነኛው የኩታ ገጠም እርሻ መሆኑን አንስተው፤ ከአጠቃላይ የመኸር አዝመራ የእርሻ ማሳ 84 ሺህ ሄክታር የሚሆነው በኩታ ገጠም እየታረሰ መሆኑን አስታውቀዋል።
ከ127 ሺህ ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሮች መከፋፈሉን በመግለፅ የግብአት አጠቃቀምን ለማሻሻል መስራት እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።
ከቀረበው ከ3 ሺህ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር በተጨማሪ አርሶ አደሮች በሳይንሳዊ መንገድ ምርጥ ዘር እንዲያዘጋጁ በማድረግ ጥቅም ላይ ማዋል መቻሉን ተናግረዋል።
በመኸር ወቅት የሚለሙ የሆርቲካልቸር ሰብሎችን በሚመለከት ከ45 ሺህ ሄክታር የሚልቅ ማሳ ለማልማት ታቅዶ ወደስራ መገባቱን በመጠቆም ከ30 ሺህ በላዩ መታረሱን አቶ ማስረሻ ተናግረዋል።
በካፋ ዞን የአዲዮ እና በቤንች ሸኮ ዞን የጉራፋርዳ ወረዳ አርሶ አደሮች በሰጡት አስተያየት፤ የአዝመራው የአየር ሁኔታ ለስራቸው ምቹ መሆኑንና ለተሻለ ውጤት እየተጉ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
በግብርና ባለሙያዎች ድጋፍና ክትትል እንዲሁም በራሳቸው ትጋት መነሻ በዘንድሮው የመኸር አዝመራ ካለፉት ዓመታት የላቀ ውጤት እንደሚያገኙ የሰብሉ አበቃቀሉም ይህንኑ እንደሚያመላክት አብራርተዋል።
ዘጋቢ፡ ዮሐንስ ክፍሌ – ከቦንጋ ጣቢያችን
More Stories
የፖሊስ አባላትና ሲቪል ሠራተኞች የገንዘብ ቁጠባና ብድር ህብረት ሥራ ማህበር ጠቅላላ ጉባኤውን አካሄደ
ኢትዮ-ኮደርስ ኢንሼቲቭ ዲጅታል ክህሎትን በማስጨበጥ ተወዳዳሪነትን የሚያሳድግ መሆኑ ተገለጸ
ስራ አጥነትን ደረጃ በደረጃ ለመቀነስና ምርታማነትን ከፍ ለማድረግ የባለድርሻ ተቋማት የተቀናጀ ርብርብ እንደሚሻ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ስራ እድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ ገለጸ