ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ በድንገተኛ መሬት መንሸራተት አደጋ ለተፈናቀሉ ወገኖች በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የተገነቡ 296 መኖርያ ቤቶችን መርቀው ለነዋሪዎች አስረከቡ

ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ በድንገተኛ መሬት መንሸራተት አደጋ ለተፈናቀሉ ወገኖች በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የተገነቡ 296 መኖርያ ቤቶችን መርቀው ለነዋሪዎች አስረከቡ

ሀዋሳ፡ ነሐሴ 22/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ በድንገተኛ መሬት መንሸራተት አደጋ ለተፈናቀሉ ወገኖች በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የተገነቡ 296 መኖርያ ቤቶችን መርቀው ለነዋሪዎች አስረከቡ።

በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ ሐምሌ 15/2016 በደረሰ ድንገተኛ የመሬት መንሸራተት አደጋ የበርካታ ዜጎች ህይወት ማለፉ ይታወሳል።

ይህን ተከትሎ መንግሥት የአካባቢው ነዋሪዎች ለሌላ አደጋ እንዳይጋለጡ በማሰብ ወደተሻለ አካባቢ እንዲዛወሩ አድርጓል።

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ለተጎጂዎች ሰብዓዊና ቁሳዊ ድጋፍ ከማድረጉ በተጨማሪ ለተጎጂዎች 296 መኖሪያ ቤቶችን አስገንብቶ ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደን ጨምሮ የክልሉና የዞኑ ከፍተኛ አመራሮችና የቀይ መስቀል ከፍተኛ አመራሮችና የአካባቢው ነዋሪዎች በተገኘበት ተመርቋል።

በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ የተገኙት ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ፤ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር አደጋው ከተከሰተበት ዕለት ጀምሮ ለተጎጂዎች አስቸኳይ ሰብዓዊ እርዳታ ከማድረጉም በላይ የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን አስታውሰዋል።

ዛሬ ለምረቃ የበቁት መኖሪያ ቤቶች የህዝቡን የመኖሪያ ቤት ችግር ከመቅረፍ አንጻር የላቀ አስተዋጽኦ እንዳላቸው ጠቅሰው፤ ተጎጂዎች ከስጋት አካባቢ ነጻ ሆነው ተረጋግተው እንዲኖሩ ያግዛል ብለዋል።

መኖሪያ ቤቶቹ በጥራትና በአጭር ጊዜ እንዲጠናቀቁ የበኩላቸውን ድርሻ የተወጡ አካላትን አመስግነዋል።

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የቦርድ ፕሬዝዳንትና የዓለም አቀፉ ቀይ መስቀልና ቀይ ጨረቃ ፌደሬሽን ቦርድ አባል አቶ አበራ ቶላ ማህበሩ ተጎጂዎችን በዘላቂነት ለማቋቋም ፕሮጀክት ቀርጾ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን ተናግረዋል።

የውስጥ አቅማችንን በማጠናከር የአባላት ቁጥር በማስፋት የጋራ ችግራችንን በጋራ ለመወጣት የጋራ ርብርብ ማድረግ ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የደቡብ ኢትዮጵያ ቅርንጫፍ ቦርድ ሰብሳቢና የክልሉ መንግስት ረዳት ተጠሪ አቶ ንጋቱ ዳንሳ፤ ማህበሩ በተለያዩ አካባቢዎች በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋ ለተጋለጡ አካላት አፋጣኝ ምላሽ በመስጠት ላይ ይገኛል ብለዋል።

በአደጋው የተፈናቀሉ የኅብረተሰብ ክፍሎችን በዘላቂነት ለማቋቋም ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የደቡብ ኢትዮጵያ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ዱንዳ፤ በደረሰው አደጋ የተለያዩ አጋሮችን በማስተባበር በርካታ ሰብዓዊና ቁሳዊ ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል።

ሁለት የውሃ ታንከሮችና ዘጠኝ የውሃ ቦኖዎችን ማስገንባቱን ጠቅሰው ለ627 አባወራና እማ ወራዎች ከ21 ሚሊየን ብር በላይ የጥሬ ገንዘብ ድጋፍ መደረጉንም አንስተዋል።

ለአካባቢው ስነ ምህዳር ተስማሚ የሆኑ የግብርና ግብዓቶች መሰራጨታቸውንም አንስተዋል።

የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ኢንጂነር ዳግማዊ አየለ በደረሰው አሰቃቂ አደጋ ሀዘናችንን በመጋራት ወገኖቻችንን ለመታደግ ቀድሞ የደረሰልን ከተደራራቢ አደጋዎች የታደገን የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ነው ብለዋል።

የገዜ ጎፋ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብርሃም ብርሃኑ፤ ማህበሩ ለተጎጂዎች በመኖሪያ ቤት፣ በውሃ መሠረተ ልማት ግንባታ እና በግብርናው ዘርፍ ውጤታማ ተግባራትን ማከናወኑን ገልጸዋል።

የአካባቢው ነዋሪዎችም ማህበሩ የተለያዩ የቁሳቁስና የገንዘብ ድጋፍ ከማድረጉም በላይ በመኖሪያ ቤት፣ በውሃ መሠረተ ልማት ግንባታ እና በግብርናው ዘርፍ ውጤታማ እንዲሆኑ ለተደረገላቸው ድጋፍ አመስግነው፤ በተደረገልን ድጋፍ የአምናውን አስከፊ አደጋ በመርሳት አዲስ የሕይወት ምዕራፍ መኖር ጀምረናል ብለዋል።

ዘጋቢ፡ አይናለም ሰለሞን – ከሳውላ ጣቢያችን