የንግድ ሥርዓትን ለማዘመን የባለድርሻ አካላት ድጋፍና ቅንጅታዊ ሥራ ወሳኝ መሆኑ ተገለፀ

የየም ዞን ንግድ እና ገበያ ልማት መምሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር በ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈፃፀምና በ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ ዝግጅት ላይ በሣጃ ከተማ ውይይት አካሂዷል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የየም ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አብርሃም ዝናቡ፤ መምሪያው በበጀት ዓመቱ የተሻለ ተግባር በመፈፀም በክልል ደረጃ የዋንጫ ተሸላሚ መሆኑን ገልፀዋል።

በቀጣይ ሰላማዊ እና ጤናማ የንግድ ሥርዓትን በመዘርጋት የዜጎችን ኑሮ ለማሻሻል መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል።

ማንኛውም ለማህበረሰቡ የሚጠቅሙ የንግድ ሥርዓቶችን ማበረታታት እና የሚጎዱ ተግባራትን ተከታትሎ ማረምና ሕጋዊ እርምጃ መውሰድ ተገቢ መሆኑን አስረድተዋል።

የንግድ ሥርዓቱን በማዘመን ተገቢውን አገልግሎት ለመሥጠትም የባለድርሻ አካላት ድጋፍና ቅንጅታዊ ሥራ ወሳኝ መሆኑንም አስገንዝበዋል።

በ2017 ዓ.ም የተከናወኑ ተግባራት ሪፖርት ያቀረቡት የየም ዞን ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ፍቃዱ በዛ፤ የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር በዞኑ ስድስት የሰንበት ገበያዎች መቋቋማቸውን ገልፀው የኦን ላየን ወይም የበይነመረብ ምዝገባ ባለፈው ዓመት ከነበረበት 66 ከመቶ ወደ 90 በመቶ ማደጉን ነው የገለፁት።

የሸማቹን መብት እና ደህንነትን ለመጠበቅ የግብይት ጥራት ቁጥጥር በማድረግ የአግልግሎት ጊዜ ያለፈባቸው ከ32 ሺህ ብር በላይ የሚገመቱ ምርቶች መወገዳቸውን ተናግረዋል።

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ምክንያት በማድረግ ተገቢ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ ያደረጉ፥ ምርት የደበቁ እና አጠቃላይ ሕገ ወጥ ተግባር የፈፀሙ ነጋዴዎች ላይ በህጉ መሰረት እርምጃ መወሰዱን ገልጸዋል።

ገበያን ለማረጋጋት የሽማቾችን የምርት አቅርቦት ለማሻሻል እና ግብረ ኃይል በማቋቋም በደረሰኝ የመገበያየት ሥርዓት እንዲዘረጋ እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል።

የሕገ ወጥ የንግድ ሥርዓት መበራከት በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ስለሚያደርስ የባለድርሻ አካላት በቅንጅት መስራት አስፈላጊ ነው ያሉት አቶ ፍቃዱ፤ ከሕገ ወጥ ንግድ ጋር ተያይዞ ያለው ቅጣት ከፍተኛ በመሆኑ መጠንቀቅ ያስፈልጋል ብለዋል።

ከጉባኤው ተሣታፊዎች መካከል አቶ ዓይነ ስሜ ቸርነት ዘርፉ እና ዘሪሁን ወ/ጊዮርጊስ ይገኙበታል።

በሰጡት አስተያየትም በዘርፉ እየተሠራ ያለው ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትና ከዚህ በላይ መስራት እንደሚጠበቅ ገልፀዋል።

የዘመነ ንግድ ሥርዓትን ለመዘርጋት ሕጋዊ መስመር ተከትሎ ማረም እና ቴክኖሎጂን በመጠቀም ግንዛቤ ማሣደግ ላይ ትኩረት ሠጥቶ መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል።

በመጨረሻም በመድረኩ ከባለድርሻ አካላት ጋር የግብ ስምምነት ተፈራርመዋል።

ዘጋቢ፡ ማሙዬ ፊጣ – ከወልቂጤ ጣቢያችን