”ሠላምን ማፅናት ለክልሉ ሁለንተናዊ ብልጽግና መረጋገጥ” በሚል መሪ ሀሳብ የክልሉ የፀጥታ ምክር ቤት ጉባኤ በሆሳዕና ከተማ መካሔድ ጀመረ

”ሠላምን ማፅናት ለክልሉ ሁለንተናዊ ብልጽግና መረጋገጥ” በሚል መሪ ሀሳብ የክልሉ የፀጥታ ምክር ቤት ጉባኤ በሆሳዕና ከተማ መካሔድ ጀመረ

ሀዋሳ፡ ነሐሴ 21/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሠላምና ፀጥታ ቢሮ ”ሠላምን ማፅናት ለክልሉ ሁለንተናዊ ብልጽግና መረጋገጥ” በሚል መሪ ሀሳብ የክልሉ የፀጥታ ምክር ቤት ጉባኤ በሆሳዕና ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።

የክልሉ ሠላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ተመስገን ካሳ መድረኩን በንግግር በከፈቱበት ወቅት እንደገለፁት፥ ሠላም ለሁሉም ነገር መሠረት ሲባል ሁሉን አቀፍ ሀገራዊ የልማት ግቦች እውን ማድረግ የሚቻለው የተረጋጋ ሠላም ሲኖር ብቻ መሆኑን አመላክተዋል።

ሠላምን ማጎልበት ከሁሉም የሚጠበቅ ነው ያሉት አቶ ተመስገን ሠላም በተቋማት ጥምረት የሚፈጠር እሳቤ ነው ብለዋል።

ኃላፊው አክለውም ሠላም፣ እኩልነትና ወንድማማችነት የሚረጋገጥበት ብቸኛ መንገድ መሆኑን ጠቁመው፥ አብሮ መልማትና ማደግ በሠላም መደፍረስ እንዳይደናቀፍ ሁሉም በቅንጅት ሊሰራ እንደሚገባ አመላክተዋል።

በክልሉ የህዝቡን ሠላም የሚያውኩ ሁኔታዎችን በጋራ በመመከት በተለያዩ ዘርፎች ፀረ ሠላም አመለካከቶችን በጋራ መመከት ይገባል ብለዋል።

ምሽት ሊከሰቱ የሚችሉ ፀረ ሠላም እንቅስቃሴዎችን በቅንጅትና በተደራጀ አኳኃን መፍታት እንደሚገባ አስረድተዋል።

የህግ የበላይነት ተረጋግጦ የፀጥታ አካላትን አቅም ማጎልበት እንዲቻል በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

በአንዳንድ የሠላም መደፍረስ በሚስተዋልባቸው አካባቢዎች ዘላቂ ሠላምን ለማስፈን በትኩረት መሠራቱን ጠቁመው፥ በ2018 የበጀት ዓመት የሚከናወኑ ሀገራዊ ጉዳዮችን በሠላማዊ ሁኔታ መከወን እንዲቻል በቅንጅት ሊሰራ እንደሚገባም አመላክተዋል።

በዚሁ መድረክ የፀጥታ ምክር ቤቱ የ2017 በጀት ዓመት አፈፃፀምና የቀጣይ በጀት ዓመት ጠቋሚ እቅድ ቀርቦ የሚገመገም መሆኑም ተመላክቷል።

በጉባኤው የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር እንዳሸው ጣሰውና የክልሉ ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ ዶ/ር ዲላሞ ኦቶሬን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ ከክልሉ ሁሉም መዋቅር የማህበራዊ መሠረት የተውጣጡ ባለድርሻ አካላት፣ የፀጥታ መዋቅር አደረጃጀቶችና ከተለያዩ አጎራባች አካባቢዎች የተውጣጡ የዘርፉ ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ የሚገኝ ሲሆን በክልሉ ዘላቂነት ያለውን ሠላም ማስፈን በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ በጥልቀት እንደሚመከር ይጠበቃል።

ዘጋቢ: አማኑኤል አጤቦ – ከሆሳዕና ጣቢያችን