በሀዲያ ዞን በደረሰ የትራፊክ አደጋ የአራት ሰዎች ህይወት አለፈ
ሀዋሳ፡ ነሐሴ 20/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በሀዲያ ዞን ምሻ ወረዳ በደረሰ የትራፊክ አደጋ የአራት ሰዎች ህይወት ማለፉ ተገለጸ::
መነሻውን ከሆሳዕና በማድረግ ወደ ጊቤ ወረዳ ሶዳ ኦሞጮራ ሰው ጭኖ ሲጓዝ የነበረ ኮድ 3 የሰሌዳ ቁጥር 19027 ሚኒባስ ተሽከርካሪ ላይ የመገልበጥ አደጋ መድረሱን የምሻ ወረዳ ፖሊስ ለደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ሆሳዕና ቅርንጫፍ ገልጿል።
አደጋው የደረሰው በሀዲያ ዞን ምሻ ወረዳ ሲኮ ቀበሌ ልዩ ስሙ ኤጌደ ተብሎ በሚጠራበት አካባቢ ከቀኑ 5፡30 መሆኑ ተመላክቷል::
ሌሎች ከባድ አደጋ የደረሰባቸው አስር ሰዎች በምሻ ወረዳና በጊቤ ወረዳ አምቡላንሶች ታግዘው ወደ ሆሳዕና ንግስት ኢሌኒ መሃመድ መታሰቢያ ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ለህክምና መላካቸውን የወረዳው ማህበረሰብ አቀፍ ወንጀል መከላከል ዘርፍ ሀላፊ ዋና ኢንስፔክተር ተስፋዬ ባህሩ ገልጸዋል።
ለደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ሆሳዕና ጣቢያ መረጃውን በስልክ ያደረሱት ዋና ኢንስፔክተር ተስፋዬ ባህሩ፤ በአደጋው የሦስት ሰዎች ህይወት ወዲያው እንዳለፈና የአንድ ሰው ግን በሞርሲጦ ጤና ጣቢያ ህክምና እየተደረገለት ሳለ ህይወቱ ማለፉን ጠቁመው፤ የአደጋው መንስኤ እየተጠራ መሆኑንም ነው የተናገሩት::
ዘጋቢ: አለቃል ደስታ – ከሆሳዕና ጣቢያችን

More Stories
በኮሬ ዞን የአስፈጻሚ መሥሪያ ቤቶች መልሶ የማደራጀት ምክክር መድረክ ተካሄደ
በአጋር ድርጅቶች የሚተገበሩ ፕሮጀክቶች የመንግስት የልማት ክፍተት በመሙላት የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ያላቸው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑ ተገለፀ
በሌማት ትሩፋት ከቤት ፍጆታ ባለፈ ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ መሆናቸውን የምዕራብ አባያ ወረዳ አርሶ አደሮች ገለፁ