ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የኑሮ ውድነት ለማረጋጋት ያልታረሱ መሬቶችን ማልማት እንደሚገባ ተገለጸ
ሀዋሳ፡ ሰኔ 07/2015 ዓ.ም (ደሬቴድ) ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የኑሮ ውድነት ለማረጋጋትና ተጨማሪ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ያልታረሱ መሬቶችን በስፋት ማልማት እንደሚገባ ተገለጸ።
የዲላ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ ማህበረሰብ አገልግሎት ዘርፍ በዘንድሮው የበልግ ወቅት ከ20 ሄክታር በላይ መሬት በወቅታዊ ሰብሎች መሸፈኑን ገልጿል።
የዲላ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ ዲን አቶ ተረፈ ሾንጦ እንደገለጹት፥ ኮሌጁ የመማር ማስተማር፣ የጥናትና ምርምርን ጨምሮ የማህበረሰብ አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን በተቋሙ ግቢ ውስጥ የሚገኘውን ሰፊ መሬት ለማልማት የተፈለገበት ዋነኛው ምክንያት፥ ምርቱን በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ የአከባቢውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ ለማድረግና በዚሁ አጋጣሚ የውስጥ ገቢን ለማሳደግ መሆኑን ጠቁመዋል።
በዘንድሮው የበልግ ወቅት ከ20 ሄክታር በላይ መሬት በወቅታዊ ሰብሎች መሸፈኑን የገለጹት አቶ ተረፈ በቂ ምርት እንደሚጠብቁና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የኑሮ ውድነት ለማረጋጋት ተጨማሪ ምርት ማምረት እንደሚያስፈልግ ተናረዋል።
በኮሌጁ የስነ-ትምህርት ሳይንስ መምህርና የማህበረሰብ አግልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ተዘራ ጌታሁን በበኩላቸው፥ አምና በተሠራው የግብርና ሥራ ማበረታቻ የውሃ መሳቢያ ፓምፕ ሽልማት ማግኘታቸው የበለጠ እንዲሰሩና በዘንድሮው የበልግ ወቅት በስፋት የተለያዩ ሰብሎችን እያለሙ እንደሚገኙ ጠቁመዋል፡፡ ምርቱ ሲደርስ ነጋዴው ከነጋዴ ሰንሰለት በመፍጠር እያስከተለ ያለውን የዋጋ ንረት ለማስቀረት ቀጥታ ለተጠቃሚዎች የሚያቀርቡበት አሰራር ለመዘርጋት ዕቅድ እንዳላቸው አስረድተዋል።
ከእርሻ ኮሚቴ አባላት መምህርት የሺሐረግ ግርማና መምህር ዘገዬ ማንደፍሮ በተቋሙ ስም የተካለለው መሬት በጣም ሰፊ ሲሆን ያለምንም አገልግሎት ቆይቶ እንደነበር አስተውሰው፥ ዘንድሮ በቆሎ በስፋት እንደተዘራበትና የዝናብ ሁኔታውም ተስፋ ሰጪ በመሆኑ ጥሩ ምርት እንደሚጠብቁ ተናግረዋል::
ከአከባቢው ማህበረሰብም ተጠቃሚ ከሆኑ አርሶ አዶሮች መካከል አቶ አብርሃም አያሌው በአሁኑ ወቅት ሰብሉ ያለበት ሁኔታ በእይታ የሚያጠግብ ነው በማለት ሁሉም ማህበረሰብ ባለው መሬት እንደዚሁ ቢያለማ መልካም ነው ሲሉ አስተያየታቸውን አጋርተውናል።
ዘጋቢ፡ ምርጫ መላኩ – ከፍስሃገነት ጣቢያችን
More Stories
በዓሉ የብሔሮችና ብሔረሰቦችን ባህልና ፀጋዎች ለማስተዋወቅ የላቀ ሚና አለው
የቀቤና ልማት ማህበር (ቀልማ) የማህበረሰቡን ሁለትናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የያዛቸው ዋና ዋና ግቦች ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አባላቱ ገለጹ
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ